የሶማሊያ ተቃዋሚዎች የፋርማጆን ፕሬዝዳንትነት ከዛሬ ጀምሮ እንደማይቀበሉ አስታወቁ
የስልጣን ዘመናቸው ዛሬ የሚያበቃውን ፋርማጆን ለመተካት አለበለዚያም በድጋሚ ለመምረጥ እንደሚያስችል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ምርጫ በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ አካባቢ ይካሄዳል በሚል ታስቦ ነበር፡፡
ተቃዋሚዎቹ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት እንዲቋቋም በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል ጠይቀዋል
የሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ከአሁን በኋላ የሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆን ፕሬዝዳንትነት እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡
እጩዎቹ የፋርማጆ የስልጣን ዘመን ዛሬ ሰኞ እ.ኤ.አ የካቲት 8 መጠናቀቁን ገልጸው ከአሁን በኋላ ፕሬዝዳንትነታቸውን እንደማይቀበሉ በጋራ ምክር ቤታቸው በኩል አስታውቀዋል፡፡
ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት (መንግስት) እንዲቋቋምም ነው የጠየቁት፡፡
የጋራ ምክር ቤቱ የሃገሪቱን የቀድሞ ሁለት ፕሬዝዳንቶች ጨምሮ ሌሎች 12 ፕሬዝዳንታዊ እጩዎችን አካቷል፡፡
ባሳለፍነው ወርሃ ህዳር ተሰብስበው የነበሩ የ14 ተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ እጩዎች ናቸው የጋራ ምክር ቤቱን የመሰረቱት፡፡
የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሼክ ሸሪፍ አህመድ ምክር ቤቱን እንዲመሩም ተመርጠዋል፡፡
ፕሬዝዳንታዊ እጩዎቹ በተያዘው ዓመት ሊካሄድ በታሰበው ሃገራዊ ምርጫ ፋርማጆን ለመቀናቀን የተዘጋጁ ተፎካካሪዎች ናቸው፡፡
ለፋርማጆ ስልጣን ከአሁን በኋላ እውቅና እንደማይሰጡ ያስታወቁት ፕሬዝዳንቱ ከአሁን በፊት በተደረሰው ስምምነት መሰረት ሃገራዊ ምርጫው ላለማካሄድ እና የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ፈልገዋል በሚል ነው፡፡
ከአሁን በኋላ የቀድሞው ፕሬዝዳንት እያሉ ለመጥራት እንደሚገደዱም ነው ያስታወቁት፡፡
ሶማሊያ ከ5 ክልላዊ መንግስታት የተዋቀረ የፌዴራል መንግስት ነው ያላት፡፡ ሆኖም ከ5ቱ 2ቱ ማለትም የፑንትላንድ እና የጁባላንድ መሪዎች ከአሁን በኋላ የፋርማጆን ፕሬዝዳንትነት እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ዓመት እንዲካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣በበርሃ አንበጣ መንጋ እና በአል ሸባብ የሽብር ድርጊቶች ምክንያት በተያዘው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ አካባቢ ይካሄዳል በሚል ታስቦ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል፡፡
ፕሬዝዳንቱን የሚሾሙት የየጎሳው ተወካዮች ባሳለፍነው ታህሳስ መመረጥ ሲገባቸውም ሳይመረጡ ቀርተዋል፡፡ ይህ ሃገሪቱን አጣብቂ ውስጥ ከቷታል፡፡
አጣብቂኙ ለአል ሸባብ ታጣቂዎች ምቹ አጋጣሚዎችን እንዳይፈጥርም ተሰግቷል፡፡
የሃገሪቱ ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽንም ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል የመሰረተ ልማትም ሆነ የገንዘብ ዐቅም እንደሌለው የኮሚሽኑ ኃላፊ ሃሊማ እስማኤል ኢብራሂም ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
የሃገሪቱ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ የስልጣን ዘመን በሚያበቃበት በዛሬው ዕለት እንደሚሰበሰብ ይጠበቃል፡፡
ሃሰን ካይሬን ተክተው በቅርቡ የተሾሙት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ሮብልም ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ይምከር አይምከር አልታወቀም፡፡ ከፕሬዝዳንት ፋርማጆም ሆነ ከጽህፈት ቤታቸው የተሰጠ መግለጫም የለም፡፡