ሁለት የአልሸባብ አዛዦች ተይዘው ለሶማሊያ ጦር መሰጠታቸውንም የኡጋንዳ ጦር አስታውቋል
የኡጋንዳ ጦር አርብ ዕለት በካምፖቻቸው ላይ ባደረሰው ጥቃት 189 የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን ተዋጊዎችን መግደሉን አስታወቀ፡፡
የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግስት ለመደገፍ እና አልሻባብን ለመዋጋት የተሰማራው የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ የኡጋንዳ ወታደሮች ይገኛሉ፡፡
የኡጋንዳ መከላከያ ሰራዊት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በታችኛው ሸበሌ ክልል ከዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ በደቡብ ምዕራብ ከ 100 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ በሚገኙት ሲጋሌ ፣ አዲሞሌ እና ካይቶይ በተባሉ መንደሮች ውስጥ ነው የአልሸባብ መሸሸጊያዎችን በመውረር የአሸባሪው ቡድን ተዋጊዎች የተገደሉት፡፡
በጥቃቱ ህይወታቸውን ካጡት 189 የቡድኑ ተዋጊዎች በተጨማሪ በርካታ ወታደራዊ ቁሳቁሶቻቸው መውደማቸውም ተገልጿል፡፡
ሁለት የአልሸባብ አዛዦች ተይዘው ለሶማሊያ ጦር መሰጠታቸውንም ነው የኡጋንዳ ጦር ያስታወቀው፡፡
የኡጋንዳ ወታደሮች “ምንም ዓይነት ኪሳራ ወይም የአካል ጉዳት አልደረሰባቸውም ፤ እንዲሁም ሲቪል ዒላማም አልተነካም” ሲል መግለጫው አመልክቷል፡፡
የአል ቃኢዳ ክንፍ በሆነው አልሸባብ ላይ የኡጋንዳ ጦር ጥቃት የፈጸመው በምድር እና በአየር ኃይል መሆኑን የጦሩ ቃል አቀባይ መግለጻቸውንም ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
ምንም እንኳን አልሸባብ በአሁኑ ወቅት ቢዳከምም ነገር ግን በማዕከላዊ እና ደቡባዊ ሶማሊያ አንዳንድ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ ይገኛል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጽማቸውን ጥቃቶችም እንደቀጠለ ነው፡፡
19 ሺ ወታደሮችን የያዘው የአፍሪካ ሕብረት ጦር በተያዘው የአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ላይ ሀገሪቱን ለቆ እንደሚወጣ ይጠበቃል፡፡
አሜሪካም በሶማሊያ የሚገኙ ወታደሮቿን በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ማስወጣቷ ይታወሳል፡፡