የሶማሊያ አጋር ለመምሰል የሚታዩ አጉል ጀብደኝነቶች ያለውን ውጥረት የሚያባብሱ ናቸው- ሬድዋን ሁሴን
አሁን እየታዩ ያሉ አካሄዶች "ለአድርባይ የውጭ አካላት ጥቅም የሚመች" እንደሆነ አስታውቀዋል
ግብጽ ከሶማሊያ ጥያቄ ከቀረበላት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጿ ይታወሳል
የሶማሊያ አጋር ለመምሰል የሚታዩ አጉል ጀብደኝነቶች ያለውን ውጥረት የሚያባብሱ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር 20 ኪሎ ሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል።
- ግብጽ ከሶማሊያ ጥያቄ ከቀረበላት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች
- የሶማሊያ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነትን "ውድቅ የሚያደረግ" ህግ ፈረሙ
ስምምነቱን ተከትሎም ሶማሊላንድ የግዛቴ አንድ አካል ናት የምትላት ሶማሊያ የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ማህሙድ በግብጽ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ ከግብጽ አቻቸው አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር ተወያይተው የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚሁ መግለጫም የግብጽ ፕሬዝዳንት አልሲሲ "የሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የመግባቢያ ስምምነት ተቀባይነት የሌለው ነው፣ ከተጠየቅን ደግሞ በሶማሊያ ላይ የሚፈጸም የሉዓላዊነት እና ግዛት አንድነት ጥቃትን ለመመከት ድጋፍ እናደርጋለን" ብለዋል።
ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በኤክስ (X) ገጻቸው፤ ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር ቀጠናዊ ውህደትን መፍጠር በሚያስችል መልኩ በትብብር መንፈስ ትሰራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ውጥረቶች ከሚያባብሱ መግለጫዎች እና ንግሮች ይልቅ ቀጣይነት ያለው ንግግር እና ውይይት የተሸ አማራጭ አድርጋ እንደምታምንም ነው አምባሳደር ሬድዋን ያስታወቁት።
የሶማሊያ አጋር በመሆን መግለጫ እየሰጡ ላሉ አካላትን በስም ባይጠቅሱም፤ “አጀንዳቸው የምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና መረጋጋት አይደለም፤ እነሱ ሊዘሩት የሚፈልጉት ጠብ እና ትርምስ ነው” ሲሉ አስታውቀዋል።
“አሁን እያየን ያነው አጉል ጀብደኝነት ውጥረትን የሚያባብስ” እንዲሁም "ለአድርባይ የውጭ አካላት ጥቅም የሚመች" እንደሆነም አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል።
“ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና ደህንነት ያላትን ቁርጠኝነት በውድ ልጆቿ ደም እና ላብ በመገበር አስመስክራለች” ሲሉም አስታውቀዋል።
አምባሳደር ሬድዋን፤ “ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ድንበር ተጋርተው የሚኖሩ ጎረቤቶች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ቋንቋ፣ ባህል እና ሕዝብ የሚጋሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።