ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ “ኤርትራ ሁሌም ከሶማሊያ ጋር ናት ለዚህም እናመሰግናለን” ብለዋል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ በኤርትራ ያደረጉትን የሁለት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት አጠናቀው ዛሬ ወደ ሞቃዲሾ ተመልሰዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ በአስመራ ቆይታቸው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት መወያየታቸውን የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሁለቱ መሪዎች በሁለትዮሽ እንዲሁም በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከግጭት ቀስቃሽ አጀንዳዎች በመቆጠብ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
የኤርትራ መንግስት ከላይ በተገለጹት የሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ በቅርቡ ሰፊ መግለጫ እንደሚያወጣም አስታውቋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ከኤርትሪያ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ “ኤርትራን በተደጋጋሚ ጎብኝቻለሁ፤ ለኛ ኤርትራ ቤታችን ናት፤ እዚህ የመጣነው ኤርትራ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች ባለችበት በሶማሊያ ሽብርተኝነትን መዋጋት ዙሪያ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገለጻ ለማድረግ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ከሰሞኑ እየተስተዋለ ስላለው ተለዋለዋጭ ሁኔታ ላይ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገለጻ ለማድረግ ወደ አስመራ ማቅናታቸውንም ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ተናግረዋል።
“ያለንበት የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና በጣም ተለዋዋጭ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ፤ “ወደ ኤርትራ የመጣሁት በአካባቢው ስለላለው ሁኔታ የሶማሊያን አቋም ላስረዳ ነው፤ ስለዚህ የዚህ ጉዞ ዋነኛው አላማ በተደጋጋሚ የምናደርገው የመረጃ መጋራት እና እርስ በርስ መነጋገር ነበር” ብለዋል።
“ኤርትራ ሁልጊዜም ከሶማሊያ ጎን ናት፤ ለዚህም ሀገሪቱነ እናመሰግናለን” ያሉት ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ፤ በተለይም “ኤርትራ ሶማሊያ ከአልሸባብ ጋር የምታደርገውን ጦርነት በመደገፍ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውታለች” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ አከልውም “ኤርትራ የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ስትደግፍ መቆየቷን እና ይህም የኤርትራ አለም አቀፍ አቋም” መሆኑን ገልጸለዋል።
“ፕሬዝዳነት ኢሳያስ ዛሬም ይህንን አረጋግጠውልኛል” ያሉ ሲሆን፤ “ለዚህም እናመሰግናላን” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃመድ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት በኋላ የመጀመሪያ የውጭ አገር ጉዟቸውን ነው በኤርትራ ያደረጉት።
የሶማሊያ ፕሬዝዳት ሀሰን ሼክ መሃመድ የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነትን ተከትሎ ከግብጽ፣ ኡጋንዳ፣ ቱርክ እና ኳታር ፕሬዝዳንቶች ጋር እንዲሁም፤ ከአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር በስልክ ተነጋግረዋል።
ባሳለፍነው እሁድም የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችውን የወደብ ሰምምነት "ውድቅ የሚያደርግ" ህግ መፈረማቸው ይታወሳል።