ኢትዮጵያ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ንግግር "ቧልት" ነው ስትል አጣጣለች
የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሽኩሪ “ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ አለመረጋጋት ምንጭ ናት” ብለዋል
በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ መካከል የነበረው የዲፕሎማሲ እና ኢኮኖሚ ግንኙነት እንደወትሮው መቀጠሉን ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል
ኢትዮጵያ የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ንግርን "ቧልት" ነው ስትል አጣጣለች።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከሶስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎ ሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነውም ተብሏል።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱን ተከትሎ የዲፕሎማሲ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ትገኛለች።
የአረብ ሊግ እና ግብጽ የኢትዮጵያን እና ሶማሊላንድን የመግባቢያ ስምምነት እንደማይደግፉ በይፋ ከተናገሩ አካላት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ትናንት በበይነ መረብ አማካኝነት በተካሄደው የአረብ ሊግ ጉባኤ ላይ የግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሜህ ሽኩሪ ኢትዮጵያ ለምስራቅ አፍሪካ አለመረጋጋት ምንጭ ናት ሲሉ ተናግረዋል።
በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም " የሳሜ ሽኩሪ ንግግር ቧልት ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ ባለፈ በሌሎችም ሀገራት ሰላም እና መረጋጋት እንዲመጣ የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ የቆየች ሀገር መሆኗንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
"ሚንስትሩ ይህን ለምን እንደሚናገሩ እረዳለሁ፣ መሰል ንግግርንም ሲናገሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም" ሲሉም ገልጸዋል።
አምባሳደር መለስ አክለውም "የአረብ ሊግ በማን እንደሚዘወር እናውቃለን፣ ያወጣው መግለጫም ሊጉ ከተቋቋማበት ዓላማ ጋር የማይሄድ ነው"ም ብለዋል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ንግግርም የግብጽ እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን የማይመጥን እንደሆነም አምባሳደር መለስ ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ሌሎች ሀገራት ካደረጉት የተለየ እንዳልሆነ እና ለኢትዮጵያ ሲሆንም የተለየ ሊሆን እንደማይችልም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ጋር ያላት የንግድ እና ዲፕሎማሲ ግንኙነት አልተቀዛቀዘም? በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ " አዲስ አባበ እና ሞቃዲሾ ግንኙነታቸው እንደቀጠለ ነው፣ ከወትሮው የተለየ ክስተት የለም" ሲሉ ተናግረዋል ።
ሌላኛው ቃል አቀባዩ መግለጫ የሰጡበት ጉዳይ በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀርጌሳ በመብረር ላይ የነበረው አውሮፕላን እንዳያርፍ መከልከሉን የሚመለከተው ጉዳይ ነው።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ቀን ላይ ፈቃድ የለውም በሚል እንዳያርፍ ተከልክሎ የነበረው አውሮፕላን ማታ ላይ በረራው መፈቀዱን እና ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባት ተፈቷል ብለዋል።