ሶማሊያ ተመድ የፖለቲካ ተልእኮውን እንዲያበቃ ጠየቀች
የሶማሊያ ፕሬዝደንት አማካሪም ሶማሊያ ከአለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለመገናኘት ከዚህ በኋላ የተመድን ድጋፍ አትፈልግም ብለዋል
ሶማሊያ ከአስርት አመታት በላይ ሲያማክራት የነበረው የተመድ የፖለቲካ ተልእኮ እንዲያበቃ ጠይቃለች
ሶማሊያ ተመድ የፖለቲካ ተልእኮውን እንዲያበቃ ጠየቀች።
ሶማሊያ በሰላም ማስከበር፣ በጸጥታ ሪፎርም እና ዲሞክራሲ ጉዳይ ከአስርት አመታት በላይ ሲያማክራት የነበረው የተመድ የፖለቲካ ተልእኮ እንዲያበቃ መጠየቋን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ለጸጥታ ምክር ቤት የተላከውን ደብዳቤ ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ ዘግቧል።
360 አባላት ያሉት በሶማሊያ የተመድ የድጋፍ ቡድን(ዩኤንሶም) በመጭው ጥቅምት ግዴታው ሲያበቃ ሶማሊያን ለቆ እንዲወጣ መጠየቁ እንዳስገረመው ሮይተርስ ዘግቧል።
የሶማሊያ ባለስልጣናት ከ1991 ጀምሮ በግጭት እና ከሁለት አስርት አመታት ለበለጠ ጊዜ ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ባለው ታጣቂ ስትታመስ የነበረችውን ሶማሊያን ለማረጋጋት እና አገልግሎቶችን ለመመለስ እየሰሩ ናቸው።
ነገርግን 17 ሚሊዮን ህዝብ ያላት የምስራቅ አፍሪካዋ ሶማሊያ አሁንም በዓለም ደሃ ከሆኑ እና የጸጥታ ስጋት ካለባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነች።
በተመድ ግዴታ ተሰጥቷቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 10ሺ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችም ቀጣናቸውን ለሶማሊያ ጦር አስረክበው በዚህ አመት መጨረሻ ይወጣሉ።
የደብዳቤውን ትክክለኛነት ሶስት የተመድ ባለስልጣናት እንዳረጋገጡለት ሮይተርስ ዘግቧል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህመድ ሞአሊን "አሁን ወደ ቀጣዩ የግንኙነታችን ምዕራፍ መሸጋገር አስፈላጊ ነው" ከማለታቸው ውጭ ተልእኮው ለቆ እንዲወጣ የፈለጉበትን ምክንያት በደብዳቤው በዝርዝር አለማስቀመጣቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የደብዳቤውን ትክክለኛነት ያረጋገጡት የሶማሊያ ፕሬዝደንት አማካሪም ሶማሊያ ከአለምአቀፉ ማህበረሰብ ጋር ለመገናኘት ከዚህ በኋላ የተመድን ድጋፍ አትፈልግም ብለዋል።
አማካሪው አክለውም "ዩኤንሶም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል፤ ነገርግን አሁን አስፈላጊነቱን አጥቷል" ሲሉ ተናግረዋል።