ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሯ ማባረሯን ገለጸች
ሀገሪቱ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከማባረር ባለፈ በፑንትላንድ የሚገኘውን ቆንስላም ዘግቻለሁ ብላለች
ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር ከወራት በፊት ያደረገችው የወደብ ስምምነት ለውሳኔው መነሻ እንደሆነ ተገልጿል
ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሯ ማባረሯን ገለጸች።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአራት ወራት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና እና ተቃውሞን ማስከተሉም አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎም ሶማሊያ የተለያዩ ዲፕሎማያው እርምጃዎችን ስትወስድ የቆየች ሲሆን፤ ዛሬ ደግሞ የኢትዮጵያን አምባሳደር ከሀገሯ ማባረሯን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ሶማሊያ በሞቃዲሾ የኢትዮጵያን አምባሳደር ያባረረች ሲሆን ለውሳኔው መነሻ የሆነው ደግሞ ከሶማሊላንድ ጋር ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ባደረገችው የወደብ ስምምነት ምክንያት ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ በፑንትላንድ እና ሶማሊላንድ ያሉ የኢትዮጵያን ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችንም ዘግቻለሁ ብላለች።
አል ዐይን አማርኛ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢዩ ተድላ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
በተያያዘ ዜና የፑንትላንድ ገንዘብ ሚንስትር መሀመድ ፋራህ የመሩት ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ ፑንትላንድ በገንዘብ ሚንስትሯ መሀመድ ፋራህ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉን ተናግረው ይህ የአዲስ አበባ ጉብኝት ከሰሞኑ ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የማይገናኝ እንደሆነ እና የጉብኝት ፕሮግራሙም የቆየ ቀጠሮ ነው ሲሉ በዛሬው ሳምንታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባደረጉት የወደብ መግባቢያ ስምምነት ምክንያት የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል።
ስምምነቱን ተከትሎም የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ መንግስት በኢትዮጵያ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምባሳደር አብዱላሂ መሀመድ ወርፋን ለምክክር ወደ ሞቃዲሾ መጥራቱን ይታወሳል።