ሶማሊያ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች እንዲዘጉ መወሰኗን ተከትሎ ሶማሊላንድና ፑንትላንድ ምን አሉ?
የሶማሊያ በሶማሊላንድና በፑንትላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ቆንስላዎች እንዲዘጉ መወሰኗ ይታወቃል
የሶማሊያ መንግስት በሞቃዲሾ የሚገኙ የኢትዮጵያ አምባሳደርም ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡም አዟል
ራስ ገዟ ሶማላንድ እና ፑንት ላንድ የሶማሊያ መንግስት በሀርጌሳ እና ጋሮዌ የሚገኙ ቆንስላዎች እንዲዘጉ ያሳለፈውን ውሳኔ መቃወማቸው ተነግሯል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ከአራት ወራት በፊት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣንና እና ተቃውሞን ማስከተሉም አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎም ሶማሊያ የተለያዩ ዲፕሎማያዊ እርምጃዎችን ስትወስድ የቆየች ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሀሙስም በኢትዮጵያ ላይ የወሰደቻቸውን እርምጃዎች የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል።
በዚህ መሰረትም በራስ ገዞቹ ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ ዋና ከተማ በሆኑት ሀርጌሳ እና ጋሮዌ ያሉ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች እንዲዘጉ ውሳኔ አሳልፋለች።
በተጨማሪም በሁለቱ ቆንስላዎች ውስጥ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችና ሰራተኞች በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶማያ ለቀው እንዲወጡ ውሳኔ ማሳለፉም ይታወሳል።
እንዲሁም የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ሞሃመድ ዋሬ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ የ72 ሰዓት ግዜ መስጠቱም ይታወቃል።
በተጨማሪም ሶማሊያ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን ለውይይት ወደ ሞቃዲሾ መጥራቷንም ሚኒስቴሩ አስታውቆ ነበር።
ይህንን ተከትሎም ራስ ገዟ ሶማሊላንድ እና ፑንት ላንድ የሶማሊያ መንግስት በሁለቱ ግዛቶች ያሉ ቆንስላዎች እዲዘጉ ያሳለፈውን ውሳኔ አውግዘዋል።
የሶማሊላንድ እና የፑንት ላንድ አስተዳደሮች የሶማሊያ መንግስት ቆንስላዎቹ እንዲዘጉ ያሳለፈውን ውሳኔ አንቀበልም ብለዋል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምክትል ሚኒስትር ሮዳ ኤሊሴይድ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "የሞቃዲሾ መንግስት የሚናገረው ምንም ይሁን ምን ቆንስላው ክፍት ሆኖ ይቆያል" ብለዋል።
የፑንትላንድ የማስታወቂያ ሚኒስትር መሀሙድ አይዲድ ድሪር ለአሜሪካ ድምፅ የሶማልኛ ቋንቋ አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፤ "የሶማሊያ ውሳኔ አይሰራም" ብለዋል።