ሞሃመድ ሁሴን ሮብል የተሾሙት የቀድሞውን የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን አሊ ካይሬን በመተካት ነው
ሶማሊያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾመች
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ (ፋርማጆ) ኢንጂነር ሞሃመድ ሁሴን ሮብልን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ሾመዋል፡፡
ሮብል በፕሬዝዳንቱ የተሾሙት የቀድሞውን የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን አሊ ካይሬን በመተካት ነው፡፡
ካይሬ ባሳለፍነው ወርሃ ሃምሌ የሃገሪቱን ምክር ቤት የመተማመኛ ድምጽ በማጣታቸው ምክንያት ከስልጣን መሰናበታቸው ይታወሳል፡፡
ከፋርማጆ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መሻከሩም ሲነገር ነበረ፡፡
ለአዲሱ ተሿሚ መልካም ምኞታቸውን የገለጹት ካይሬ ሁሉም ሶማሌያውያን ከጎናቸው እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
በ1950ዎቹ መገባደጃ ለአካባቢ ጋልሙዱግ በተሰኘው ክልል ሆብዮ በተባለ አካባቢ የተወለዱት ሲቪል መሃንዲሱ ሮብል በዓለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት ኃላፊነት ስር ሆነው ላለፉት 14 ዓመታት ሃገራቸውን ማገልገላቸውን ከፕሬዝዳንቱ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አሁንም እንዲካሄድ ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ሃገር አቀፍ ምርጫ ለማቀላጠፍ መስራት ይጠብቃቸዋል፡፡ ይህን ለማቀላጠፍ በቀጣዮቹ 30 ቀናት ውስጥ መንግስት እንደሚመሰርቱም ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው ያመሰገኑት ሮብልም ሃገራቸው በሽግግር ላይ መሆኗን በመግለጽ ህዝባቸውን በታማኝነት እንደሚያገለግሉ በትዊተር የማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡