“በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ የማትሳተፈው ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት” -የሶማሊያ መከላከያ ሚንስትር
እስከ 2028 የሚቆየው አትሚስን የሚተካው አዲሱ ልዑክ በመጪው ጥር ወር ስራውን ይጀምራል
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በቅርቡ በአዲሱ ልዑክ ውስጥ በሚሳተፉ ሀገራት ተዘዋውረው መወያየታቸው ይታወሳል
በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ይተካል በተባለው አዲስ የሰላም አስከባሪ ሃይል የማትሳተፈው ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ እንደሆነች የሶማሊያ መከላከያ ሚንስትር ተናገሩ፡፡
በባላፈው አመት መጀመርያ ላይ ራስ ገዟ ሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ የወደብ የመግባባያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ውጥረት ውስጥ የሚገኘው የአዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሻሻል አልታየበትም፡፡
“ኢትዮጵያ ሉአላዊነቴን ጥሳለች” ስትል የምተከሰው ሶማሊያ “የመግባባያ ስምምነቱ ካልተሰረዘ ኢትዮጵያ በአዲሱ ልዑክ እንድትሳተፈ አልፈቅድም” በሚለው አቋሟ ጸንታለች፡፡
የሶማሊያ የመከላከያ ሚንስትር አብዱልቃድር መሀመድ ኑር “እስካሁን በአዲሱ የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ ውስጥ የማትሳተፍ ብቸኛዋ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ማረጋገጥ እችላለሁ” ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ (አሚሶም) በሚል ስያሜ ከ2007 ጀምሮ ከበርካታ ሀገራት የተውጣጡ የአፍሪካ ህብረት ወታደሮች በሶማሊያ ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡
ከሚያዝያ 1 ቀን 2022 ጀምሮ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮ አትሚስ በመቀየር እስካሁን የዘለቀው ልዑክ በፈረንጆቹ አመት መጠናቀቂያ የስራ ጊዜው ያበቃል፡፡
በመጪው ጥር ወር የስራ ጊዜው የሚጠናቀቀውን (አትሚስ) የሚተካው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍ ተልዕኮ (AUSSOM) በአትሚስ ስር የነበሩትን 20 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ወደ 12 ሺህ ዝቅ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ለ17 አመታት በሀገሪቱ የተሰማራው ልዑክ የሶማሊያን መንግስት በመገልበጥ ሀገሪቱን ለማስተዳደር የሚፈልገውን በሽብርተኛነት የተፈረጀውን አልሸባብ በመዋጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ጥር አንድ ስራውን የሚጀምረው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ጥምረት እስከ 2028 በሚኖረው ቆይታ የጸጥታ እና ደህንነት ስራውን በሂደት ለሶማሊያ መንግስት በማስረከብ ከሀገሪቱ ሙሉ በሙሉ ለቆ እንደሚወጣ ይጠበቃል፡፡
የሶማሊያ መከላከያ ሚንስትር የቀድሞ ዳይሬክተር ሶንኮር ጌይሬ ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ሞቃዲሾ ከብሔራዊ ጥቅሞቿ እና ከደህንቷ ጋር በተያያዘ በልዑኩ ውስጥ የሚሳተፈውን ሀገር የመምረጥ ሙሉ መብት አላት” ብለዋል፡፡
ባለፈው ወር የኤርትራ ፣ ሶማሊያ እና ግብጽ መሪዎች በአስመራ የጸጥታ ትብብር ስምምነት መፈጸማቸው ይታወሳል፤ ከዚህ ባለፈም ካይሮ በአዲሱ ልዑክ ለማሳተፍ እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት 5 ሺ ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ ለመላክ ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች፡፡
ካይሮ በቀጠናው አሰማራዋለሁ ያለችው ጦር በአካባቢው በሚገኘው ጥምር ጦር ላይ በትጥቅ እና በሌሎች አሰላለፎች አጠቃላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ስጋቶች እየተሰሙ ነው፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮችን ለመቀበል በነበረው መድረክ ንግግር ያደረጉት የሶማሊያ የመከላከያ ሚንስትር “አዲሱን የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ የሚቀላቀሉ አዲስ ሀገራትን እና ከነባሮቹ የማይቀጥሉትን በቅርቡ በግልጽ ይፋ እናደርጋለን” ብለዋል፡፡
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀመድ ኬንያ ፣ ጂቡቲ እና ዩጋንዳን ጨምሮ በልዑኩ ውስጥ በሚሳተፉ ሌሎች ሀገራት ጋር ለመወያየት በቅርቡ የዲፕሎማሲ ጉዞ አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡
የስራ ጊዜው እየተጠናቀቀ በሚገኝው አትሚስ ውስጥ ከ3ሺ የማያንሱ የኢትዮጵያ ወታደሮች የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ አካል ሆነው አልሸባብን በመዋጋት ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት ባላቸው የሁለትዮሽ ስምምነት ከ5 እስከ 7 ሺህ የሚጠጉ የኢትዮጵያ ወታደሮች በተለያዩ ክልሎች ሰፍረዋል።
ቡሩንዲ ፣ ዩጋንዳ ፣ ኬንያ እና ጂቡቲ ለአትሚስ ወታደሮችን በመላክ በሶማሊያ ሰላም ማስከበር ከሚሳተፉ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።