የግብጽ፣ ሶማሊያና ኤርትራ መሪዎች በአስመራ የሶስትዮሽ ምክክር አደረጉ
ምክክሩ የሶስቱን ሀገራት ትብብር በሚያሳድጉና በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለይፋዊ ጉብኝት አስመራ የገቡት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው
የግብጽ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ፕሬዝዳንቶች በአስመራ የሶስትዮሽ ምክክር አደረጉ።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ የሶስትዮሽ ምክክሩን ዝርዝር አጀንዳዎች ይፋ ባያደርጉም የሀገራቱን ትብብር የሚያሳድጉና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ በትናንትናው እለት ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አስመራ መግባታቸውና ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲም በዛሬው እለት አስመራ ሲገቡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ መሻከሩ ይታወሳል።
ስምምነቱ ሉአላዊነቴን የተዳፈረ ነው በሚል የተቃወመችው ሞቃዲሾ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰምምነት እንድትሰርዝ ከማሳሰብ ባሻገር የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዳለች።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድም ወደ ኤርትራ እና ግብጽ ደጋግመው በመመላለስ ድጋፍ ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ዳግም ቅራኔ ውስጥ የገባችው ግብጽ ለሶማሊያ ድጋፏን በማሳየት በሀምሌ ወር ከሞቃዲሾ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች።
ካይሮ የጦር መሳሪያዎች እና ወታደሮችን ወደ ሶማሊያ መላኳን የሚያመላክቱ ዘገባዎች መውጣታቸውም አይዘነጋም፤ ምንም እንኳን ሶማሊያ ዘገባውን ብታስተባብልም።
በአስመራ የመጀመሪያውን ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አስመራ የገቡት ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከሶማሊያ እና ኤርትራ አቻዎቻቸው ጋር ባደረጉት የሶስትዮሽ ምክክር ወቅታዊው የሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ፍጥጫ ዋነኛ አጀንዳ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የፕሬዝዳንት አልሲሲ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ የአስመራው ምክክር “በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር ሰላምና መረጋጋት ማስፈን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል” ብሏል።
የግብጽ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ መሪዎች የሶስትዮሽ ምክክር ያደረጉት የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ግንኙነት እየቀነሰ በመጣበት ወቅት መሆኑንም ፍራንስ 24 አስነብቧል።
የኢትዮጵያ አየርመንገድ ባለፈው ወር ወደ አስመራ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡ ይታወሳል።
ሁለቱ ሀገራት የመደበኛ የስልክ አገልግሎትን ዳግም ካስጀመሩ ከሰባት ዓመታት በኋላ መቋረጡንም በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ለአልአይን አማርኛ ተናግረዋል።