ሶማሊያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በ72 ሰአታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ዲፕሎማቱ ከሀገር እንዲወጡ የታዘዙት ከዲፕሎማሲ ስራዎች የሚጣረስ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው
ሶማሊያ ቀደም ሲል የኢትዮጵያን አምባሳደር ሙክታር መሀመድ ዋሬን ማባረሯ ይታወሳል
ሶማሊያ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት በ72 ሰአታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ አዘዘች።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ በአማካሪነት ወይም በካውንስለርነት የሚሰሩት አሊ መሀመድ አደም የተባሉት ዲፕሎማት በ72 ሰአት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መታዛቸውን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ አለመግባባት ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የራስ ገዟ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ባለፈው የፈረንጆቹ አዲስ አመት እለት የወደብ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ነበር።
ስምምነቱ አለምአቀፍ ህግን እና ሉአላዊነቷን እንደሚጥስ የገለጸችው ሶማሊያ በመጋቢት ወር የኢትዮጵያን አምባሳደር ሙክታር መሀመድ ዋሬን ማባረሯ ይታወሳል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ዲፕሎማቱ ከሀገር እንዲወጡ የታዘዙት ከዲፕሎማሲ ስራዎች የሚጣረስ ተግባር ውስጥ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው።
የዲፕሎማቱ ድርጊት ዲፕሎማቶች ያሉባቸውን ሀገር ህግ ማክበር እና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት መቆጠብ አለባቸው የሚለውን የቬናን የዲፕሎማቲክ ድንጋጌ የሚጥስ ነው ያለው ሚኒስቴሩ ሉኣለዊነትን ለመጠብቅ ሲባል ይህ እርምጃ መወሰዱን ገልጿል።
ቱርክ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን አለመግባባት በንግግር ለመፍታት፣ የሁለቱን ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተናጠል በሁለት ዘር አነጋግራለች።ነገርግን ባለፈው መስከረም ሊካሄድ የነበረው ሶስተኛ ዙር ንግግር ሳይካሄድ ቀርቷል።
የሁለተኛው ዙር ንግግር መጠናቀቅን አስመልክቶ የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ባወጡት መግለጫ ቀጣይ ውይይቶችን ለማድረግ የሚያስችሉ መሻሻሎች መኖራቸውን ገልጸው ነበር።
ነገርግን በተለይ በአባይ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ያለቸው ግብጽ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳ መዘገቡን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ መግጫ ተለዋውጠዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ነሀሴ ባወጣው መግለጫ ሶማሊያ ከውጭ ኃይሎች ጋር በመሆን ቀጣናውን ለማተራመስ እየሰራች ሲል ከሷል። መግለጫው አክሎም ኢትዮጵያዊ ይህን ጉዳይ በዝምት እንደማታልፈውም አስጠንቅቋል።
ከግብጽ እና ቱርክ ጋር ወታደራዊ ስምምነት የፈጸመችው ሶማሊያ ደግሞ ህገወጥ የጦር መሳሪያ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ፑንትላንድ እየገባ ነው የሚል ክስ ማቅረቧ ይታወሳል።