የሶማሊያ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነትን "ውድቅ የሚያደረግ" ህግ ፈረሙ
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል
ሰምምነቱ ሉኣለዊነትን የሚጥስ ነው የምትለው ሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች
የሶማሊያ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነትን "ውድቅ የሚያደረግ" ህግ መፈረማቸውን ገለጹ።
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችውን የወደብ ሰምምነት "ውድቅ የሚያደርግ" ህግ መፈረማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ተገንጣይ የሆነችው ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድትከራይ እና በምትኩ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል ነው።
ይህ ስምምነት ሶማሊላንድን የራሷ ሉአላዊ ግዛት አድርጋ በምታያት ሶማሊያ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት መሀሙድ በትናትናው እለት "ዛሬ ማታ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የፈረሙትን ህገወጥ የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ የሚያደርግ ህግ ፈርሚያለሁ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።
ፕሬዝደንቱ "ይህ ህግ በአለምአቀፍ ህግ መሰረት አንድነታችንን፣ ሉኣዊነታችንን እና የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው" ብለዋል።
ህጉ ምን እንደሚል እና መቼ በፖርላማ እንደሚጸድቅ ፕሬዝደንቱ አልገለጹም።
ሰምምነቱ ሉኣለዊነትን የሚጥስ ነው የምትለው ሶማሊያ፣ በጉዳዩ ላይ ምክክር ለማድረግ በኢትዮጵያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ጠርታለች።
ፕሬዝደንቱ በዚሁ ጉዳይ በተሰበሰበው ፖርላማ ፊት ቀርበው እንደናገሩት የተፈረመው ስምምነት ህግን የሚጥስ እና ተፈጻሚ የማይሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ ሌሎች ሀገራት ከሶማሊያ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የፈረሙት ስምምነት የሚጎዳው ሀገርም ሆነ የሚጥሰው ህግ እንደሌለ ገልጿል።
መንግስት ኢትዮጵያ ለባህር ኃይል የሚሆን የጦር ሰፈር ስታገኝ፣ ሶማሊላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምታገኝ ተስማምቷል።
መንግስት ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና መስጠትን በተመለከተ ኢትዮጵያ አጢና አቋም ትወስዳለች ብሏል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቀይ ባህር የህልውና ጉዳይ መሆኑን እና ይህንንም ለማግኘት መደራደር ያስፈልጋል ካሉ በኋላ የባህር በር ጉዳይ አጀንዳ ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት የኢትዮጵያን ጥያቄ በበጎ እንዲያዩት፣ያ ካልሆነ ግን ቆይቶ ሊፈናዳ የሚችል የጸጥታ ችግር እንደሚሆን ማሳሰባቸው ይታወሳል።
የአትዮጵያ ህዝብ በ2030፣ 150 ሚሊዮን እንደሚደርስ እና ይህ ህዝብ ወደብ አልባ መሆን አይችልም ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የአፍሪካ ህብረት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ እንዲረጋጉ፣ ውጥረቱን ሊያባብሱ ከሚችሉ እርምጃዎች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርቧል።
ህብረቱ የአባል ሀገራትን የግዛት አንድነትን እና ሉአላዊነት ማክበር አስፈላጊ ነው ብሏል።