ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመስከረም ወር ሁለተኛ ዙር ድርድር ለማድረግ ተስማሙ
የሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ መዲና አንካራ ያደረጉት ድርድር ተጠናቋል
ቱርክ፥ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን አስታውቃለች
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመስከረም ወር ሁለተኛ ዙር ድርድር ለማድረግ ተስማሙ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታየ አጽቀስላሴ እና የሶማሊያው አቻቸው አህመድ ሙአለም ፊቂ ጋር ትናንት በአንካራ መክረዋል።
በቱርክ የተካሄደውን ንግግር መጠናቀቅን አስመልክተው መግለጫ የሰጡት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን፥ ሀገራቱ ልዩነታቸውን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ” ልዩነታቸውን ለመፍታት ሁለተኛውን ዙር ድርድር በፈረንጆቹ መስከረም 2 2024 በአንካራ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የገለጹት።
“የጉዳዩ ውስብስብነት ሚስጢር አይደለም፤ እናም ተጨማሪ ማብራሪያ እንሻለን” ያሉት ፊዳን፥ የትናንቱ ንግግር በቀጣይ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አብራርተዋል።
የቱርክ የደህንነት ምንጮቹን ጠቅሶ ቲአርቲ እንዳስነበበው ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ትናንት በአንካራ ድርድር ያደረጉት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በግንቦት ወር በአንካራ ጉብኝት ሲያደርጉ ለፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን ባቀረቡት የአደራድሩን ጥያቄ መሰረት ነው።
በአንካራው ድርድር የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት መሻከር ምክንያት የሆነችው ራስ ገዟ ሶማሊላንድ አልተጋበዘችም።
የቱርክ ግንኙነት ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ
ከኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ጋር ግንኙነቷን ያጠናከረችው ቱርክ በአንካራ በሚካሄደው የሀገራቱ ድርድር የአመቻቺነት ሚና ብቻ ይኖረኛል ብላለች።
ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በፈረንጆቹ 2011 በሞቃዲሾ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ አንካራ የሶማሊያ የጸጥታ ሃይሎችን ማሰልጠን የጀመረች ሲሆን፥ ትምህርትቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችንም ስትገነባ ቆይታለች።
ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ ስምምነት ከደረሱ ከአንድ ወር በኋላም ቱርክና ሶማሊያ የ10 አመት የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
ስምምነቱ ቱርክ የሶማሊያን የባህር ሃይል ለማጠናከርና የሽብር ስጋትን በጋራ ለመመከት የሚያስችል ነው ተብሎ ነበር።
የሶማሊያን የባህር ክልል ለመጠበቅ ትውላለች የተባለች የቱርክ መርከብም በቅርቡ ሶማሊያ መድረሷ ይታወሳል።
አንካራ በአፍሪካ ግዙፍ የጦር መንደር ያላት በሶማሊያ ነው፤ ለሞቃዲሾ የምታደርገው ድጋፍም በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ለማሳደግ ያግዛታል።
ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋርም ጠንካራ የንግድ ትስስር የመሰረተች ሲሆን፥ በትግራይ ክልል ጦርነት ሲካሄድም ለኢትዮጵያ ድሮኖችን መሸጧ የሚታወስ ነው።