ሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅናን የሚያስፈጽም ግብረ ሀይል በሚኒስቴር ደረጃ አቋቋመች
ግብረ ሀይሉ ከኢትዮጵያ ጋር የተደረሰውን የመግባቢያ ስምምነት እና ሌሎች ለሶማሊላንድ እውቅና የሚያስገኙ ስትራቴጂዎች ላይ አተኩሮ ይሰራል
የመግባብያ ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል
ሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅናን ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የሚያስፈጽም ግብረ ሀይል በሚኒስቴር ደረጃ ማቋቋሟን አስታወቀች፡፡
ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ የግብረ ሀይሉ መቋቋም ሀገር ለመሆን ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ እርምጃ ነው ብላለች፡፡
ግብረ ሀይሉ እውቅና ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶችን በስትራቴጃዊ ጉዳዮች በመደገፍ ሂደቱን ለማፋጠን ይሰራል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር በተደረሰው የመግባብያ ስምምነት መሰረት ሂደቱ የሚፋጠንበትን እና ወደ ተግባር በሚለወጥበት ሁኔታ ላይ አተኩሮ ይሰራል ነው የተባለው፡፡
ሶማሊያ እንደራሷ ግዛት አድርጋ የምታያት ሶማሊላንድ ራሷን ብታስተዳድርም አለምአቀፍ የሀገርነት እውቅናን ማግኘት አልቻለችም።
ከወራት በፊት ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ በተፈራረሙት የመግባብያ ስምምነት ኢትዮጵያ በኤደን ባህረ ሰላጤ ለ50 አመታት በሊዝ ኪራይ የሚቆይ 20 ኪሎሜትሮች የሚረዝም የባህር ጠረፍ እንድታገኝ እና በምላሹ አዲስ አበባ ለሶማሊላንድ እውቅና እንድትሰጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት መፈጠሩ አይዘነጋም።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በውቅቱ ባወጣው መግለጫ "የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው" ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
ቀጥሎም የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የደረሰችውን የወደብ ሰምምነት "ውድቅ የሚያደርግ" ህግ ፈርመዋል፡፡
ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ባለብዙ ወገን ድርጅቶች እና ሀገራት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በወደብ ስምምነቱ ምክንያት የተፈጠረው ውጥረት ወደ ግጭት እንዳያመራ ሲያስጠነቅቁ ሰንብተዋል።
የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ስለ ወደብ ስምምነቱ ባደረጉት ንግግር የአትዮጵያ ህዝብ በ2030፣ 150 ሚሊዮን እንደሚደርስ እና ይህ ህዝብ ወደብ አልባ መሆን አይችልም ነበር ያሉት።
የመግባብያ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ወደ ቀጣይ ምዕራፎች እንደሚገባ የተነገረለት ስምምነት ዙርያ እስካሁን እምብዛም ጠንከር ያሉ የውሳኔ ሀሳቦች አልተሰሙም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በስምምነቱ ዙርያ በቅርቡ በቱርክ ድርድር መጀመራቸው ይታወሳል፡፡