የግል ንግድ ባንኮች አንድ ዶላርን እስከ 121 ብር ገዝተው እስከ 123 ብር እየሸጡ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መሃል ያለው ልዩነት እንዲቀራረብ ባሳሰበ ማግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ ታይቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ህዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የባለፈውን ሳምንት ተመን አስቀጥሏል። አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ119.2044 ብር እየገዛ ሲሆን፤ በ121.5885 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አንድ ዶላርን በ121.0980 ብር ገዝቶ በ123.5200 ብር እየሸጠ እንደሚገኝ በእለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመኑ ላይ አመላክቷል።
ጎህ ቤቶች ባንክ የትናንቱን የምንዛሬ ተመን ሲያስቀጥል የዶላር መግዣ ዋጋው 121.5204 ብር ነው። 123.9508 ብር ደግሞ የአንድ ዶላር መሸጫ ዋጋ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ጠቁሟል።
ዳሽን ባንክ የህዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም እለታዊ የምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ የትናንቱን ዋጋ አስቀጥሏል። በዚህም አንድ ዶላርን በ120.8506 ብር እየገዛ በ123.2676 ብር እየሸጠ መሆኑን ገልጿል።