ሶማሊላንድ ግብጽ ወታደሮቿን በሶማሊያ ማሰማራቷን አጥብቃ እንደምትቃወም ገለጸች
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የግብጽ ጦር በሶማሊያ መሰማራቱ ለአፍሪካ ቀንድ ደህንነት ስጋት ነው ብሏል
ኢትዮጵያ በትላንትናው ዕለት አዲስ አምባሳደር ወደ ሶማሊላንድ ልካለች
ሶማሊንድ ግብጽ በሶማሊያ እደረገች የምትገኝውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አጥብቃ እንደምትቃወም አስታወቀች፡፡
ራስ ገዟ ሀገር ከሰሞኑ በሶማሊያ የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ማረፋቸውን ተከትሎ ካይሮ በአካባቢው እያደረግች የምትገኝው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለሶማሊያ እንዲሁም ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ጸጥታ እና ደህንነት ስጋት ነው ብላለች፡፡
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ባወጣው መግለጫ የውጭ ሀይሎች በጎረቤት ሶማሊያ መስፈር ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ሰላምን ለማስፈን ሲደረግ የነበረውን ጥረት የሚጎዳ ነው ሲል ግልጿል፡፡
አለምአቀፉ ማህበረሰብ የግብጽን አደገኛ እንቅስቃሴ እንዲያወግዝ የጠየቀው መግለጫው “የእኛንም ሆነ የጎረቤቶቻችንን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል የማንኛውንም የውጭ ሀይል ጣልቃገብነት አንታገሰም” ብሏል፡፡
የቀጠናው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሀገራት ቀጠናውን ወደ ከፋ አለመረጋጋት ውስጥ ከሚከቱ አካሄዶች በመታቀብ ልዩነቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴሩ ጠይቋል፡፡
መግለጫው አክሎም በአካባቢው ያለው ያልጸና ሰላም መሰል ድርጊቶች ውጥረቶችን በማባበስ አስከፊ ቀውስ ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጾ ሶማሊላንድ መሰል ድርጊቶችን ከዳር ቆሟ እንደማትመለከት አቋሙን አንጸባርቋል
ግብጽ እና ሶማሊያ በቅርቡ የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ከቀናት በፊት የግብጽ እቃ ጫኝ የጦር አውሮፕላኖች በሶማሊያ መታየታቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ መንግሥት ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል በሚል ቅሬታውን መግለጹ ይታወሳል፡፡
ሌሎች ተዋናዮች ቀጠናውን ሲያተራምሱ ኢትዮጵያ በዝምታ አትመለከትም ያለው መግለጫው ሶማሊያ አካባቢውን ሰላም ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ብታተኩር የተሻለ እንደሚሆን አሳስቧል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷ ሲሻክር፥ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ያለችው ግብጽ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግኝኙነት እያጠናከረች ትገኛለች፡፡
በቅርቡ በደረሱት ወታደራዊ ስምምነት መሰረትም ግብጽ የሶማሊያን የመከላከያ እና የደኅንነት አቅም ለማሻሻል የሚያስችሉ ተጨማሪ ድጋፎችን፣ ስልጠናዎችን እንደምታደርግ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ካይሮ ሠራዊቷን ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ሶማሊያ ለመላክ ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።
ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያ ለሀርጌሳ አዲስ አምባሳደር ሾማለች፡፡ አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ለሶማሊ ላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ የሹመት ደብዳቤ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የተላከ መልዕክት አድርሰዋል።
ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ ከአምባሳደር ተሾመ ጋር በነበራቸው ውይይት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የጸጥታ ጉዳዮች፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማጠናከርና የወደፊት ትብብር ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጿል።