ሶማሊያ ከግብጽ ጋር ያደረገችው ወታደራዊ ስምምነት በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል?
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያለው ጉዳይ ብሔራዊ ደህንነቷን የሚጎዳ ከሆነ ማንኛውንም እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ገልጿል
በሊባኖስ ያሉ 150 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድድ ሁኔታ የለም ተብሏል
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ወቅት ከጋዜጠኞች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የግብጽ እና ሶማሊያ ወታደራዊ ስምምነቶች በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አንድምታ ይኖረዋል? የሚለው ዋነኛው ነበር።
እንዲሁም የሶማሊያን ጸጥታ እና ደህንነት ለማስጠበቅ በሚል በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የተሰማራው ሰላም አስከባሪ ጦር (አትሚስ) ተልዕኮ የፊታችን ታህሳስ ያልቃል።
የሶማሊያ ጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት አሁንም የሚፈለገውን አቅም አለመገንባታቸውን ተከትሎ አትሚስን ተክቶ እንደ አዲስ በሚዋቀረው ሰላም አስከባሪ ስር ግብጽ ጦር ለማዋጣት ፍላጎት ማሳየቷ እና የሶማሊያ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ጦር በአዲሱ ተልዕኮ ስር እንዳይካተት መፈለጋቸውስ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል? የሚለው ጥያቄም ለአምባሳደር ነብዩ ተነስቶላቸዋል።
አምባሳደር ነብዩ በምላሻቸው ላይ እንዳሉት "ሶማሊያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፣ እንደ ሀገር ከፈለገችው ጋር ማንኛውንም አይነት ስምምነት መፉራረም ትችላለች። ከግብጽ ጋር ያደረገችው ወታደራዊ ስምምነት ኢትዮጵያን አያስጨንቅም" ብለዋል።
የፊታችን ታህሳስ ወር ላይ የሚያበቃው የአትሚስ ተልዕኮን የሚተካ አዲስ ሰላም አስከባሪ ሀይል ለማቋቋም ውይይት እየተደረጉ እንደሆነ የተናገሩት አምባሳደር ነብዩ ሰላም አስከባሪ ሀይል ማዋጣት የሚፈልጉ ሀገራት ፍላጎታቸውን እንዲገልጹ በተላለፈው ጥሪ መሰረት ግብጽ ጥያቄ ካቀረቡ ሀገራት አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ተልዕኮ ውስጥ መሳተፏ ካላት የሰላም ማስከበር ልምድ እና አሁንም መቀጠል መፈለጓ የበለጠ የሚጠቅመው ሶማሊያን ነውም ብለዋል።
ይሁንና የሰላም አስከባሪ ጦር የማዋጣት ፍላጎት ያላቸው ሀገራት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ያስቀመጠው ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ አፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና ሌሎችም አካላት የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጡበታል ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም "ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ብዙ ድጋፍ እንዳደረገ፣ የህይወት መስዋዕትነት እንደመክፈሏ እና በሶማሊያ የሚደረገው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነት እና ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ከተገኘ ማናቸውንም እርምጃ ትወስዳለች" ብለዋል።
አዲሱ የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ በአካባቢው አዲስ ውጥረት በሚፈጥር መልኩ እንዳይሆን ኢትዮጵያ ጥረት እንደምታደርግም ተገልጿል።
ሌላኛው በመግለጫው ላይ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ምክንያት በመካከለኛው ምስራቅ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ደህንነት ጉዳይ ነው።
እስራኤል በቴህራን የሐማሱን የፖለቲካ ቢሮ ሀላፊ እስማኤል ሀኒየህን መግደሏን ተከትሎ ኢራን ከሂዝቦላህ ጋር በመሆን በስራኤል ላይ የአጸፋ እርምጃ ትወስዳለች መባሉን ተከትሎ በሊባኖስ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የደህንነት ስጋት ተደቅኖባቸዋል ተብሏል።
አምባሳደር ነብዩ እንዳሉት በሊባኖስ 150 ሺህ ያህል ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ገልጸው አሁን ላይ ኢትዮጵያዊያኑ ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድድ ሁኔታ የለም ብለዋል።
ይሁንና በአካባቢው ያለው ሁኔታ ተለዋዋጭ በመሆኑ ኢትዮጵያዊያን አስቀድመው ንብረቶቻቸውን መልክ እንዲያሲዙ አምባሳደር ነብዩ አሳስበዋል።
የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ከተባባሰ ግን ከሊባኖስ እና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ዜጎቻችንን ልናስወጣ እንችላለንም ብለዋል።