ግብጽ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳ ተነገረ
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ግብጽና ሶማሊያ በዚህ አመት ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል
ግብጽ በሚቀጥለው አመት ስራ ለሚጀምረው በሶማሊያ ለሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮች የማዋጣት ፍላጎት እንዳላት ገልጻለች
ግብጽ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳ ተነገረ።
ግብጽ ከሶሰት አስርት አመታት በኋላ በትናንትናው እለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳን ሮይተርስ ሶሰት የዲፕሎማቲክ እና የሶማሊያ መንግስት ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ ግብጽና ሶማሊያ በዚህ አመት ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ የግዛቷ አካል አድርጋ ከምታያት ሶማሊላንድ ጋር የደረሰችው የወደብ ስምምነት፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ በሊዝ ኪራይ ለ50 አመታት ያህል ለባህር ኃይል እና ንግድ የሚያገልግል የባህር ጠረፍ እንድታገኝ እና በምላሹ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ ያስችላል ተብሎ ነበር።
የሶማሊያ መንግስት ስምምነቱ ህገወጥ መሆኑን እና ተግባራዊ እንዳይሆን ሁሉንም አማራጭ እንደሚጠቀም መግለጹ ይታወሳል።
በስምምነቱ ቁጣዋን ያሰማችው ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር በማባረር ዲፕሎማሲያዊ ቅራኔው እንዲባባስ አድርጋዋለች።
በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ባለው ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገባችው ግብጽ ስምምነቱን አውግዛው ነበር።
ግብጽ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሞቃዲሹ ጋር የደህንነት ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን በሶማሊያ ለሚሰማራው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ወታደሮች ለመላክ ፈቃደኝነቷን ገልጻለች።
ሶማሊያ ስምምነቱ የማይሰረዝ ከሆነ በሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት መሰረት አልሸባብን ለመዋጋት በሶማሊያ ሰፍረው የሚገኙትን 10ሺ ገደማ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እንደምታስወጣ አስፈራርታለች።
የጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ የያዙ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች በትናንትናው እለት ሞቃዲሹ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፋቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
ሮይተርስ ካናገራቸው ዲፕሎማቶች አንዱ ሶማሊያ ከግብጽ የጦር መሳሪያ በማስገባት እና ከኢትዮጵያ በመቃረን "በእሳት እየተጫወተች ነው" ብለዋል። ሮይተርስ በጉዳዩ ዙሪያ የሶማሊያ እና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን እንዲሁም የኢትዮጵያን መንግስት ቃል አቀባይ አስተያየት ማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።
ግብጽ በሚቀጥለው አመት ስራ ለሚጀምረው በሶማሊያ ለሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ወታደሮች የማዋጣት ፍላጎት እንዳላት በዚህ ወር መጀመሪያ የወጣው የአፍሪካ ህብረት መግለጫ አስታውቋል።
ቱርክ ከባለፈው ሀምሌ ወር ወዲህ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በሶማሊላንድ የወደብ ስምምነት የተፈጠረውን አለመግባባት እንዲፈቱ ሁለት ጊዜ ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር እንዲያደርጉ መድረክ አመታችታለች።
በሁለቱ ዙር ንግግር ጉልህ የሚባል ውጤት ባይመጣም፣ መሻሻሎች መኖራቸውን ቱርክ እና የሁለቱ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ንግግሩ ካበቃ በኋላ መሰጠት መግለጫ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሶስተኛው ዙር ንግግር በሚቀጥለው ወር ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ወደብ የህልውናዋ ጉዳይ መሆኑን እና ጎረቤት ሀገራትም ይህንኑ ሊረዷት እንደሚገባ ስትገልጽ ቆይታለች።