ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግስት ቀጠናውን ለማተራመስ ከውጭ ሃይሎች ጋር እየሰራ ነው ስትል ከሰሰች
ግብጽ ወደ ሶማሊያ የጦር መሳሪያ በላከች ማግስት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አውጥቷል
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ከሻከረ በኋላ የካይሮና ሞቃዲሾ ትብብር ተጠናክሯል
ኢትዮጵያ የሶማሊያ መንግስት ቀጠናውን ለማተራመስ ከውጭ ሃይሎች ጋር በትብብር እየሰራ ነው ስትል ከሰሰች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፥ በሶማሊያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ሚኒስቴሩ መግለጫውን ያወጣው ግብጽ ከሶሰት አስርት አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሶማሊያ የጦር መሳሪያ መላኳ ከተነገረ በኋላ ነው።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ጋር በተፈራረመችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት ከሶማሊያ ጋር ግንኙነቷ ሲሻክር፥ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ቅራኔ ውስጥ ያለችው ግብጽ ለሶማሊያ ድጋፏን አሳይታለች።
ግብጽ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሞቃዲሾ ጋር የደህንነት ስምምነት የተፈራረመች ሲሆን በሶማሊያ ለሚሰማራው አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ወታደሮች ለመላክ ፈቃደኝነቷን መግለጿም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ግብጽን በስም ባይጠቅስም በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አትሚስ) ሽግግር ሂደት ሳይጠናቀቅ በሞቃዲሾ አዲስ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ለማሰማራት የሚደረገው ለቀጠናው አደገኛ ነው ብሏል።
የአፍሪካ ህብረትም ሆነ የመንግስታቱ ድርጅት በታህሳስ ወር ተልዕኮው የሚጠናቀቀው አትሚስ በሚተካበት ሂደት ዙሪያ ዝግጅት እያደረጉ በሚገኙበት ወቅት ቀጠናው ታይቶ ወደማይታወቅ ችግር እየገባ ነው ሲልም ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ እና ለአትሚስ ተልዕኮ ወታደሮች ያዋጡ ሀገራት ስጋታቸውን ደጋግመው ቢያቀርቡም ከቁብ አለመቆጠሩንም በማከል።
ኢትዮጵያ ውጥረት ለሚያባብሱ መግለጫዎች ምንም ምላሽ እንዳትሰጥ ሲጠበቅ ቆይቷል ያለው መግለጫው፥ ወታደሮቿ የከፈሉት መስዋዕትነት ዝቅ ተደርጎ እንዲታይ ተከታታይ ጥረት ሲደረግ መክረሙንም አብራርቷል።
መግለጫው “ኢትዮጵያ ሌሎች ተዋናዮች ቀጠናውን የሚያተራምስ እርምጃ ሲወስዱ በዝምታ አትመለከትም” ያለ ሲሆን፥ ክልላዊ እና አለማቀፍ የሽብር ሃይሎች ላይ የተገኘውን ድል አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴን በፍጹም አንታገስም ብሏል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ መንግስት ጋር የገባችበትን ሰጣ ገባ በንግግር ለመፍታት ጥረት ማድረጓንና በንግግሮቹ ተስፋ ሰጪ ነገሮች መታየታቸውን በመጥቀስም፥ የሶማሊያ መንግስት የሰላም ጥረቶቹ ፍሬ እንዲያፈሩ ከመጣር ይልቅ ቀጠናውን ለማተራመስ ከሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ጋር ተባብሯል ሲልም ከሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ሁሉም በአዲሱ (የሶማሊያ) የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ለመሳተፍ የተዘጋጁ ሀገራት በቀጠናው የሚገኙና ለአትሚስ ወታደሮች ያዋጡ ሀገራትን ስጋት ማጤን ይኖርባቸዋል” ብሏል።
ኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነቷንት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ የቀጠናው ዋና ዋና ሁነቶችን በአንክሮ እየተከታተለች መሆኑን ያብራራው መግለጫው “ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በቀጠናው ውጥረት እያባባሱ ነው” ያላቸውን ሃይላት ግን በስም አልጠቀሰም።
ከሶማሊያ መንግስት ጋር አሁንም በንግግር ልዩነቱን ለመፍታት ዝግጁነቱን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት፥ አለማቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ደህንነት ላይ የተጋረጠውን አደጋ እንዲቀለብስ ጥሪ አቅርቧል።