ሴቶች በአማካይ 63ኛ ዓመታቸው ከፍተኛ ሀብት የሚሰበስቡበት ዓመት እንደሆነ ተገልጿል
የዓለም ሀብት ሪፖርት ተቋም በሴት ባለጸጋዎች ዙሪያ ያስጠናውን የጥናት ውጤት ይፋ ያደረገ ሲሆን በዚህ ጥናት መሰረት በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት የሴት ባለጸጋዎች ሀብት የ6 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡
ይሄንን ተከትሎም የዓለም ሴት ባለጸጋዎች ሀብት የ41 ነጥብ 8 ትሪሊዮን ዶላር ቅናሽ ሲያሳይ የሀብት ዓለመመጣጠን ከጾታ አንጻር መስፋቱ ተገልጿል፡፡
በዓለም ካሉ ሀብቶች ውስጥ በሴቶች የተያዙት 11 በመቶ ያህል ብቻ ሲሆን ይህም ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል ክፍያ አለመኖር፣ ስልጠና እና የስርዓተ ጾታ አመለካከት ችግሮች ለሀብት ዓለመመጣጠኑ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ የዓለም ኢኮኖሚክ ጉባኤ ጥናት ያስረዳል፡፡
ሴቶች በህይወት ዘመናቸው በአማካኝ 63ኛ ዓመታቸው ብዙ ሀብት የሚያከማቹበት ዓመት ሲሆን ወንዶች ደግሞ በ65 ዓመታቸው ላይ ብዙ ሀብት ይይዛሉ ተብሏል፡፡
ሴቶች ካሏቸው ሀብቶች ውስጥ 25 በመቶ ያህሉን በውርስ እንደሚያገኙ ይሄው ጥናት ይስረዳል፡፡
ፈረንሳዊቷ ፍራንሶይዝ ቤትንኮርት የ75 ቢሊዮን ዶላር ባለቤት ሲሆኑ የዓለማችን ቀዳሚ ሴት ባለጸጋ ናቸው፡፡
አሜሪካዊቷ የዎልማርት ኩባንያ ባለቤቷ አሊስ ዋልተን ደግሞ በ60 ቢሊዮን ዶላር ሁለተኛዋ የዓለማችን ሴት ባለጸጋ ሲሆኑ የቀድሞው የአማዞን ባለቤቱ ጄፍ ቤዞፍ ባለቤት የነበሩት ማክኔዚ ስኮት በ53 ቢሊዮን ዶላር ሶስተኛዋ ባለጸጋ እንስት ናቸው፡፡
ከዓለማችን ባለጸጋ ሴቶች ውስጥ 45 በመቶዎቹ ሀብታቸውን ያገኙት በተሰማሩበት ስራ ውጤታማ በመሆናቸው ሲሆን ቀሪ ሀብታቸውን ደግሞ በውርስ እና በሌሎች መንገዶች እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዓለም ባለጸጋ ሴቶች በአብዛኛው በአሜሪካ፣ ጀርመን እና ቻይና ያሉ ሲሆን በቻይና ካሉ ባለሀብት እንስቶች ውስጥ 82 በመቶዎቹ በራሳቸው ለፍተው ያገኙት ሀብት ነው ተብሏል፡፡
በአሜሪካ ደግሞ 51 በመቶዎቹ ባለጸጋ ሴቶች ሀብታቸውን በራሳቸው ድካም ሲያገኙ በጀርመን ደግሞ 15 በመቶዎቹ ብቻ ሀብታቸውን በራሳቸው ለፍተው ያገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
በዓለም ላይ ያሉ ሴት ባለጸጋዎች ከወንዶች ጋር ሲነጻጸሩ ሴቶች ከንዶች ከእጥፍ በላይ የተሻለ የበጎ አድራጎት ስራዎችን እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
እንዲሁም ሴት ባለጸጋዎች ከወንድ ባለጸጋዎች ጋር ሲነጻጸሩ ጥሬ ገንዘባቸውን በባንኮች ሲያስቀምጡ ወንዶች ደግሞ እንደ ቤት እና የመሳሰሉት ነገሮች ላይ ያውላሉ፡፤
እንዲሁም ሴት ባለጸጋዎች ቅንጡ እና ውድ ጌጣጌጦችን ሲሸምቱ ወንድ ባለጸጋዎች ደግሞ ዘመናዊ ጀልባዎችን እና ውድ የግል ጄቶችን በመሸመት ወደር የላቸውም ሲል ይሄው ጥናት ጠቁሟል፡፡