“የአለማችን ሀብታሙ የኔቢጤ” ሀብት 1 ሚሊየን ዶላር ተገምቷል
ህንዳዊው ባህራት ጄን በሙምባይ ጎዳናዎች ምጽዋት እየለመነ ቤት ገዝቷል፤ የሚከራዩ ሱቆችም አሉት
ግለሰቡ በልመና ገንዘብ ሀብት ቢያከማችም አሁንም ከአመታት ልማዱ ሊላቀቅ አልቻለም
በህንድ ሙምባይ ጎዳናዎች ከሰዎች ምጽዋት የሚጠይቀው ባህራት ጄን የአለማችን ሃብታሙ የኔቢጤ ነው ተብሏል።
ህንዳውያን 100 ሩፒ ለማግኘት ረጅም ስአት በሚሰሩባት ሙምባይ ጄን በየቀኑ ከ2 ሺህ እስከ 2 ሺህ 500 ሩፒ ያገኛል ብሏል ኢኮኖሚክ ታይምስ በዘገባው።
ጄን በከተማዋ ሰዎች በሚርመሰመሱበት ቻትራፓቲ ሻቫጂ በተባለው የባቡር ጣቢያ ለአመታት ምጽዋት በመጠየቅ አሳልፏል።
ከደጋግ ህንዳውያን የሚያገኘው ድጋፍም ሀብት እንዲያከማች እንዳደረገው ነው ዘገባው የሚጠቅሰው።
አጠቃላይ ሃብቱም ከ1 ሚሊየን ዶላር በላይ እንደሚገመት የሚገልጸው ኢኮኖሚክ ታይምስ፥ በሙምባይ ባለሁለት መኝታ ቤት እና በየወሩ 30 ሺህ ሩፒ የሚከራዩ ሁለት ሱቆች እንዳሉት ያብራራል።
በወር ከ60 ሺህ ሩፒ (731 ዶላር) እስከ 75 ሺህ ሩፒ (914 ዶላር) የሚያገኘው ግለሰቡ፥ ረጅም አመታትን ተምረው የተሻለ ገቢ ያለው ስራ ከተቀጠሩ ህንዳውያን የበለጠ ገቢ እንደሚያገኝም ያነሳል።
ምንም አይነት የአስኳላ ትምህርት ያልተከታተለው ባህራት ጄን ኑሮን ለመግፋት የጀመረው ልመና ሃብት አከማችቶም ሊቆም አልቻለም።
ተምረው ስራ የጀመሩ ልጆቹ መለመኑን እንዲያቆም ቢወተውቱትም ክፉ ልማድ ሆኖበት አሁንም የእርዱኝ ተማጽኖውን ማሰማቱን ቀጥሏል ነው የተባለው።
የህንድ መገናኛ ብዙሃን ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ “ሀብታሙ የኔቢጤ” በሚል በተደጋጋሚ ይዘውት የሚወጡት ዜናም ሊያሳፍረው አልቻለም።
ሳይሰራ በሚያገኘው ምጽዋት ሚሊየነር ለሆነው ባህራት ጄን የሰው ፊት እንደ እሳት ይጋረፋል የሚባለው ብሂል አይሰራም፤ እንደውም “እርዱኝ” እያለ መማጸኑ ሱስ ሳይሆንበት አይቀርም ይላል ኢኮኖሚክ ታይምስ በዘገባው።