“አፍሪካ በተመድ ጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ አለማግኘቷ አሳዛኝ ነው” የደቡብ አፍሪካ እና ሴኔጋል መሪዎች
ጠ/ሚር ዐቢይም አፍሪካ በጸጥታው ም/ቤት ውክልና ያስፈልጋታል ብለዋል
ሮበርት ሙጋቤ በ26ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ የተመድ የጸጥታው ም/በት እንዲሻሻል ጠይቀው ነበር
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ እና የሴኔጋሉ አቻቸው ማኪ ሳል አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ ውክልና አለማግኘቷ ፍትሃዊ እንዳልሆነ አስታወቁ፡፡
ራማፎዛ በዳካር በተካሄደው የአፍሪካ የሰላም እና ጸጥታ ጉባዔ ላይ አፍሪካ በጸጥታው ም/ቤት በተገቢው መንገድ እንድትወከል መደረግ አለበት ብለዋል፡፡ “ፍትሃዊ የሆነ ነገር እንፈልጋለን” ያሉት ራማፎዛ የአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ሕዝብ ሃሳቦች ሃሳብና አመለካከት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ባላቸው ኃይሎች ሊሰማ እንደማይችልም ተናግረዋል፡፡
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል በበኩላቸው 54 የአፍሪካ ሀገራት በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ አለማግኘታቸው ትክክል እንዳልሆነ ገልጸው ይህንንም ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከሌሎቹ ሀገራት ጋር በመሆን እንደሚታገሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ይህንን የአፍሪካ ሀገራት በተመድ የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን ሃሳብ መቀላቀላቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ አንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ሕዝብ ያለው የአፍሪካ አህጉር በተመድ የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ መቀመጫ ሊኖረው እንደሚገባ በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡
የአፍሪካን አህጉር የሚመለከቱ ሀሳቦችና ውሳኔዎች ያለ አህጉራዊ ውክልና ሊፈታ እንደማይችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናረዋል፡፡
የቀድሞው የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርቶ ሙጋቤ አዲስ አበባ በፈረንጆቹ 2016 በተካሄደው 26ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተመድ የጸጥታው ም/ቤት ማሻሻያ እንዲያደርግ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ሮበርቶ ሙጋቤ በህብረቱ ጉባኤ ላይ ለተገኙት የተመድ ዋና ጸኃፊ ባን ኪሙን ነበር ም/ቤቱ ማሻሻያ እንዲያደርግ የተናገሩት፡፡