የአፍሪካ ህብረት በአባል ሀገራቱ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ ጠየቀ
እርምጃው ወደፊት በግልጸኝነት በጋራ ለመስራት የማያስችል እንደሆነም ነው የገለጸው
ህብረቱ እገዳው አሉታዊ ምጣኔ ሃብታዊና ሌሎች ተጽዕኖዎችን በማድረስ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል
የአፍሪካ ህብረት ከአዲሱ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ ‘ኦሚክሮን’ጋር በተያያዘ በአባል ሀገራቱ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ ጠየቀ፡፡
አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መኖሩን ለማረጋጋጥ ላስቻለው ውጤታማ የቁጥጥር እና ምርምር ስራቸው ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋናን ያደነቀው ህብረቱ መረጃውን መላው ዓለም እንዲጋራው ማድረጋቸውን አወድሷል፡፡
የአዲሱን ቫይረስ የስርጭት እና ሌሎች ባህሪያት ለማወቅ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ በማስታወስም የቫይረሱ የስርጭት ሁኔታ ከፍተኛ ነው በሚል ያለ በቂ መረጃዎች በደቡብ አፍሪካ ሀገራት ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ ተገቢ እንዳይደለ አስታውቋል፡፡
እገዳዎቹ በዜጎች የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን አሳድረዋል ያለው ህብረቱ አስፈላጊ የህክምና አቅርቦቶችን ለማሟላት ጉድለቶች መፈጠራቸውን እና ተመራማሪዎች ተጨማሪ ጥናቶችን ለማድረግ መቸገራቸውን ገልጿል፡፡
ደቡብ አፍሪካ የተጣለብኝ የጉዞ ክልከላ “በጉልበት የተጫነና የማይጠቅም ነው” ስትል ተቃወመች
ገና ለገና የቫይረሱን ሁኔታ በመስጋት ዓለም አቀፍ የጤና ስምምነቶች በሚያዙት መሰረት መረጃውን ባጋሩ አባል ሃገራቱ ላይ እንዲህ ዐይነት የቅጣት እርምጃ መወሰዱ የማይደገፍና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ነው የገለጸው፡፡
ወደፊት በግልጸኝነት በጋራ ለመስራት የማያስችልና አፍሪካንም ሆነ መላው ዓለምን ለተጨማሪ የጤና ስጋቶች የሚዳርግ ነውም ብሏል ህብረቱ፡፡
በመሆኑም በአባል ሃገራቱ ላይ የተጣለው የጉዞ እገዳ በአስቸኳይ እንዲነሳ ጠይቋል፡፡
ፍትሐዊ የክትባቶች ስርጭት መኖር ለወረርሽኙ ቁጥጥርም ሆነ ለህክምናው እንደሚበጅ በማስታወስም የክትባት ተደራሽነቱን ለማስፋት በትብብር እንዲሰራ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የህብረቱ የበሽታዎች ቅኝት እና ቁጥጥር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ከአሁን ቀደምም ድርጊቱን ኮንኖ ተመሳሳይ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የጉዞ እገዳውን አፓርታይድ ሲሉ መኮነናቸውም አይዘነጋም፡፡