የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት፤ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ኦባሳንጆ ገለጻ ተደረገለት
በስብሰባው በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተካፍለዋል
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ ዛሬ ያደረገውን አስቸኳይ ስብሰባ አጠናቋል
የአፍሪካ ህብረት የጸጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ ኦባሳንጆ ገለጻ ተደረገለት፡፡
ህብረቱ ዛሬ ጥቅምት 29 ቀን 2014 ዓ/ም አስቸኳይ ዝግ ስብሰባ አካሂዷል፡፡ ስብሰባው በበይነ መረብ የተካሄደ ነው፡፡
በስብሰባው የህብረቱ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዲዎዬ፣ የህብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴገን ኦባሳንጆ፣ በአፍሪካ ህብረት የግብጽ ቋሚ ተወካይ መሃመድ ጋድ እና በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ተሳትፈዋል፡፡
ስብሰባው የተካሄደው በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምክርና የአፍሪካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴገን ኦባሳንጆን ገለጻ ለማድመጥ ነበር፡፡
ይህንንም የምክር ቤቱ የአል ዐይን አማርኛ የመረጃ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሲሰበሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡
ኦባሳንጆ የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ ከአውሮፓ ሕብረት ም/ቤት ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ
ህብረቱ በምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ ሀገራት ያጋጠሙ የጸጥታ ችግሮችን እንዲያሸማግሉ የወከላቸው ኦባሳንጆ ትናንት ወደ ትግራይ አቅንተው በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡
አቶ ጌታቸው ረዳን መሰል የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችም ይህንኑ አሳውቀዋል፡፡
አፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ “ሁሉም ወገኖች ተኩስ አቁመው ለውይይት እንዲቀመጡ” በድጋሚ አሳሰቡ
በአፍሪካ ህብረት የኢትዮጵያ ተወካይ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ በተሳተፉበት በዚህ ስብሰባ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ከመከረና የኦባሳንጆን ገለጻ ካደመጠ በኋላ ያለው ወይ ያስቀመጠው ቀጣይ አቅጣጫ እንዳለ የታወቀ ነገር የለም፡፡
አል ዐይን አማርኛ ስለዚህ ጉዳይ ለማወቅ ያደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡
ነገር ግን ምክር ቤቱ የተሰበሰበበትን ጉዳይ የተመለከተ መግለጫን እንደሚያወጣ ለአል ዐይን ገልጿል፡፡
ባሳለፍነው አርብ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ አስቸኳይ ስብሰባን ያደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ግጭቶች ቆመው ተኩስ ለማቆም የሚያስችል ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡