ደቡብ ኮሪያ አዲስ የእድሜ አቆጣጠር ህግ አወጣች
የሀገሪቱ ዜጎች እንደተወለዱ አንድ አመት ሆናቸው ተብሎ ይመዘገብ የነበረ ሲሆን፥ ጥር ወር እንደገባ ደግሞ ሁለተኛ አመታቸውን ይይዛሉ
የእስያ ሀገራት የተለየ የእድሜ አቆጣጠር ስርአትን የሚከተሉ ሲሆን አብዛኞቹ ግን አሻሽለውታል
ደቡብ ኮሪያ ሁለት አይነት የእድሜ አቆጣጠር ስልት አላት።
የመጀመሪያው ህጻናት እንደተወለዱ አንድ አመት ሆናቸው ተብሎ የሚመዘገብበት ስርአት ነው።
ሌላኛው ደግሞ ጥር ወር በገባበት የመጀመሪያው ቀን እድሜ የሚጨመርበት ስርአት ነው።
በዚህም መሰረት በታህሳስ ወር መጨረሻ የተወለደ ወይም የተወለደች ህጻን በመጀመሪያው ህግ አንድ አመት በሁለተኛው ደግሞ (ጥር እንደገባ) አዲስ አመት ተጨምሮለት ወይም ተጨምሮላት በአንድ ቀን ልዩነት ሁለት አመት ይሆነዋል ወይም ይሆናታል ማለት ነው።
ሃንኩክ የተባለው የሀገሪቱ የጥናት ተቋም ባለፈው አመት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ከአራት ደቡብ ኮሪያውያን ሶስቱ ጥንታዊውን የእድሜ አቆጣጠር እንደማይፈልጉት አመላክቷል።
የሀገሪቱ ህግ አውጪዎችም በታህሳስ ወር 2023 አለማቀፉን የእድሜ አቆጣጠር ስርአት ለመከተል ውሳኔ ማሳለፋቸው የሚታወስ ነው።
ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የእድሜ አቆጣጠር ስርአቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚተገበረውን (ከልደት ቀን ከአንድ አመት በኋላ አንድ አመት ይዟል) ስርአት ለመከተል ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ተነግሯል።
ደቡብ ኮሪያውያንን ከሌላው አለም ሰዎች በአንድ ወይም በሁለት አመት የሚያስረጀው የእድሜ አቆጣጠር ስልት ከዛሬ ጀምሮ እንዲሰረዝ መደረጉንም አስታውቀዋል።
የቆየው ስርአት “አላስፈላጊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ” ማስከተሉንም ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት።
ለአብነትም ከኢንሹራንስ ክፍያ እና የመንግስት ድጎማ ፕሮግራሞች ጋር በተያያዘ የእድሜ ጉዳይ ሲያከራክር መቆየቱን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
የተለያዩ የእስያ ሀገራት እድሜን የሚቆጥሩበት ስርአት የተለየ ቢሆንም አብዛኞቹ አሻሽለውታል።
ጃፓን በ1950 ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በ1980ዎቹ አለማቀፉን የእድሜ አቆጣጠር መከተል መጀምራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።