የደቡብ ኮሪያውያን ሴቶች የውልደት ምጣኔ ከዘጠኝ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨመረ
ሴኡል ዜጎቿ ትዳር እንዲመሰርቱ የምታቀርበው ማበረታቻ ወጣት ጥንዶች ጎጆ ቀልሰው ልጆችን እንዲወልዱ እያነቃቃ ነው ተብሏል

በአሁኑ ወቅት 51.7 ሚሊየን ህዝብ የሚኖርባት ደቡብ ኮሪያ፥ በ2072 ህዝቧ ወደ 36.2 ሚሊየን ዝቅ እንደሚል ተተንብዩዋል
የደቡብ ኮሪያ የውልደት ምጣኔ ከዘጠኝ አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጭማሪ አሳየ።
ለውልደት ምጣኔው ማደግ በጋብቻ የሚተሳሰሩ ጥንዶች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ ማድረጉ ተገልጿል።
የውልደት ምጣኔ ማለት አንዲት ሴት በህይወት ዘመኗ በአማካይ ምን ያህል ልጆች ልትወልድ ትችላለች የሚለውን የሚያመላክት ሲሆን፥ የደቡብ ኮሪያውያን ሴቶች የውልደት ምጣኔ ከ2015 ወዲህ በከፍተኛ ደረጃ እያሽቆለቆለ ነው።
ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 2024 ግን ከ2023ቱ ጭማሪ ማሳየቱን የሀገሪቱ ስታስቲክስ ተቋም አስታውቋል። የሀገሪቱ የውልደት ምጣኔ በ0.03 አድጎ 0.74 ሆኖ መመዝገቡንም ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ ምጣኔው ሴኡልን ከአለማችን ሀገራት የመጨረሻው ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት ነው።
ሀገራት የህዝብ ቁጥራቸው በተረጋጋ ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ የሴቶች አማካይ የመውለድ ምጣኔ 2 ነጥብ 1 መሆን እንዳለበት ይነገራል።
ደቡብ ኮሪያ የህዝብ ቁጥሯ በተከታታይ አመት መቀነሱን መቀጠሉን ተከትሎ ጎጆ መቀለስ ለከበዳቸው ጥንዶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን በማቅረብ ልጆችን እንዲወልዱ እየመከረች ትገኛለች።
ባወጁት የወታደራዊ ህግ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ፍርድቤት የቀረቡት ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል "ብሄራዊ የስነ ህዝብ ቀውስ" አጋጥሟል በሚል የውልደት ምጣኔውን የሚያሳድግ አዲስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማቋቋማቸው የሚታወስ ነው።
በሀገሪቱ በጋብቻ እና ልጆችን በመውለድ ዙሪያ ያለው ማህበረሰባዊ አመለካከት እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያነሳው የደቡብ ኮሪያ ስታስቲክስ፥ በ2024 ጋብቻ በ14.9 በመቶ ማደጉን ገልጿል። ይህም ከ1970 ወዲህ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡንም በመጥቀስ።
ደቡብ ኮሪያ የውልደት ምጣኔው እኝዲያድግ ያደረገው ጋብቻ እድገት ቢያሳይባትም የህዝብ ቁጥሯ ግን ለአምስተኛ ተከታታይ አመት ቀንሷል። ሴጆንግ የተሰኘችው የአስተዳደር ከተማ ብቻ ናት የህዝብ ቁጥር እድገት የተመዘገበባት።
ባለፈው አመት የሞቱት አዲስ ከተወለዱት ህጻናት በ120 ሺህ እንደሚልቁ ነው የተገለጸው።
በአሁኑ ወቅት 51.7 ሚሊየን ህዝብ የሚኖርባት ደቡብ ኮሪያ፥ በ2072 ህዝቧ ወደ 36.2 ሚሊየን ዝቅ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የስታስቲክስ ተቋሙ ትንበያ አመላክቷል።