ደቡብ ኮሪያ በራሷ ተይዞ የቆየውን ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ ክብረወሰን ሰበረች
በሀገሪቱ የአንዲት ሴት ልጅ አማካይ የመውለድ ምጣኔ ወደ 0 ነጥብ 78 ዝቅ ብሏል
ከሚወለደው ይልቅ የሚሞተው የሚበዛባት ደቡብ ኮሪያ፥ የህዝብ ቁጥሯ እያሽቆለቆለ መሄዱን ቀጥሏል
የአለማችን ዝቅተኛውን የውልደት ምጣኔ ያስመዘገበችው ደቡብ ኮሪያ በራሷ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን አሻሽላለች።
ደብ ኮሪያውያን ሴቶች የመውለድ ምጣኔያቸው በ2021 ከነበረበት 0 ነጥብ 81 በ2022 ወደ 0 ነጥብ 78 ዝቅ ብሏል።
ሀገራት የህዝብ ቁጥራቸው በተረጋጋ ሁኔታ ይቀጥል ዘንድ የሴቶች አማካይ የመውለድ ምጣኔ 2 ነጥብ 1 መሆን እንዳለበት ይነገራል።
በደቡብ ኮሪያ ግን አንዲት ሴት አንድ ልጅ የመውለድ እድሏ እንኳን ዝቅ ያለ ሆኗል።
ከ2015 ጀምሮ እየቀነሰ የመጣው የውልደት ምጣኔ በ2022ትም አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል ነው የተባለው።
በዚሁ አመት 249 ሺህ ህጻናት የተወለዱባት ሴኡል፥ የ372 ሺህ 800 ሰዎችን ህልፈት አስተናግዳለች፤ ይህም በ2021 ከነበረው የህዝብ ቁጥሯ ላይ ከ120 ሺህ በላይ ቅናሽ እንዲያሳይ ምክንያት ሆኗል።
ደቡብ ኮሪያ በ2020 ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከተወለዱት የበለጠው።
የተለያዩ መውለድን የሚያበረታቱ ውሳኔዎችን ያሳለፈችው ሴኡል፥ ባለፉት 16 አመታት የህዝብ ቁጥሯን ከፍ ለማድረግ 200 ቢሊየን ዶላር ወጪ አድርጋለች።
ይሁን እንጂ ከባህል፣ ኑሮ ውድነት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ዜጎች የመውለድ ፍላጎታቸው ሊስተካከል አልቻለም።
በወሊድ ምክንያት ለሚወጡ ወላጆች የሚሰጥ እረፍት እና የድጎማ ገንዘብ እንዲጨመር በመንግስት የተላለፉ ውሳኔዎችም ደቡብ ኮሪያን በየአመቱ የህዝብ ቁጥሯ እየቀነሰ ከመሄድ አልታደጋትም።
ይህም የአዛውንቶቿ ቁጥር እየጨመረ ቀጣዩ ተረካቢዋ ትውልድ እንዳይጠፋ ከፍ ያለ ስጋትን እየፈጠረ መሆኑን ሲ ኤን ኤን አስነብቧል።
ጃፓን እና ቻይናም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ እንደሚገኙም መገለጹም አይዘነጋም።