በ2050 ከአለም ሀገራት 75 በመቶው ዝቅተኛ የውልደት ምጣኔ ያስመዘግባሉ- ጥናት
በ1950ዎቹ አንዲት ሴት በአማካይ 5 ልጆችን ትወልድ የነበረ ሲሆን፥ በ2021 ወደ ሁለት ዝቅ ብሏል
የበለጸጉት ሀገራት የውልደት ምጣኔያቸው በእጅጉ ሲቀንስ፥ በደሃ ሀገራት ህጻናት በብዛት እየተወለዱ ይገኛሉ
የአለም ሀገራት የውልደት ምጣኔ በ21ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ የህዝብ ቁጥሩን በነበረበት ማስቀጠል የማያስችል መሆኑ ተመላከተ።
ላንሴት የተሰኘው ታዋቂ የህክምና ጆርናል ላይ የወጣው ጥናት ከአለም ሀገራት ከ75 በመቶ በላዩ በ2050 ዝቅተኛውን የውልደት መጠን እንደሚያስመዝግቡ ተንብዩዋል።
በ2100 የውልደት ምጣኔያቸው የመጨረሻው ዝቅተኛ የሚሆንባቸው ሀገራት ቁጥርም 198 እንደሚደርስ ነው ጥናቱ ያሳየው።
የህዝብ ቁጥር በተስተካከለ ሁኔታ እንዲቀጥል አንዲት ሴት ቢያንስ ሁለት ልጆችን መውለድ ይኖርባታል።
እንስቷ ራሷንና ባለቤቷን ተክታ ካላለፈች የህዝብ ቁጥሩ ባለበት መቀጠል ስለማይችል ዝቅተኛው የውልደት ምጣኔ 2 ልጅ ነው ተብሎ ተደጋግሞ ይነሳል።
በ1950ዎቹ አንዲት ሴት በህይወት ዘመኗ በአማካይ አምስት ልጆችን ትወልድ እንደነበር ስታስቲካዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይሁን እንጂ በ2021 ይህ የውልደት ምጣኔ ወደ 2 ነጥብ 2 (ሁለት ልጆች) ዝቅ ብሏል።
በ22ኛው ክፍለዘመን መግቢያ አለማቀፍ የውልደት ምጣኔው ወደ 1.59 ያሽቆለቁላል ተብሎ እንደሚገመት ጥናቱ አመላክቷል።
ከ1950 እስከ 2021 በአለማቀፍ ደረጃ የተደረጉ የህዝብ ቆጠራ እና ሌሎች የዳሰሳ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ የተካሄደው ጥናት፥ የውልደት ምጣኔያቸው የተሻሉ ሀገራት ደሃ ሀገራት ናቸው ብሏል።
በአለማቀፍ ደረጃ በየእለቱ ይህቺን አለም ከሚቀላቀሉት ህጻናት 75 ከመቶው ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት እናቶች የሚገኙ ናቸው፤ ከግማሽ በላዩ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ይወለዳሉ።
እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓንና ቻይና ያሉ ሀገራት መውለድን ለማበረታታት ቢሊየን ዶላሮችን ቢያፈሱም የውልደት ምጣኔያቸው ከ1 ነጥብ 4 ሊያልፍ አልቻለም።
በእስያ ሀገራት አዛውንቶች እየበዙና ወጣት የሰው ሃይል እየጠፋ የመሄዱ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ቁጥራቸው መቀነስም አሳሳቢ ሆኖባቸዋል።
ህጻናት በብዛት እየተወለዱባቸው የሚገኙ ሀገራት ደግሞ እንዴት እናሳድጋቸው የሚለው ያሳስባቸዋል።
aXA6IDMuMTM2LjE1NC4xMDMg ejasoft island