የተከሰሱት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ከእስር ተፈቱ
የሀገሪቱ ህገመንግስታዊ ፍርድቤት ዮን ሱክ የል ወደ ስልጣናቸው ይመለሱ ወይም ይባረሩ በሚለው ጉዳይ በቀጣይ ቀናት ውሳኔ ያሳልፋል ተብሏል

ዮን በደቡብ ኮሪያ በስልጣን ላይ እያሉ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ የመጀመሪያው መሪ ናቸው
የተከሰሱት የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ከአንድ ወር በላይ እስር በኋላ ተለቀቁ።
የሴኡል ሴንትራል ዲስትሪክት ፍርድቤት በዮን ላይ የወጣው የእስር ማዛዣ ጊዜውን ያልጠበቀና ከህጋዊነት አንጻር ተቀባይነት የለውም የሚል ውሳኔ በትናንትናው እለት አሳልፏል።
አቃቤ ህግም ይህን ውሳኔ ተቃውሞ ይግባኝ ባለመጠየቁ በሴኡል ታስረውበት ከቆዩበት ስፍራ እንዲወጡ መደረጉን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
ዮን በጠበቃቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት "ለሀገሬ ህዝብ አንገቴን ዝቅ አድርጌ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ" ብለዋል።
38 ሺህ የሚገመቱ የዮን ደጋፊዎች በሴኡል ደስታቸውን ለመግለጽ መውጣታቸው ተገልጿል።
ከ1 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ደቡብ ኮሪያውያን ደግሞ መፈታታቸውን ተቃውመው አደባባይ መውጣታቸውን ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘግቧል።
በታህሳስ ወር ለስድስት ስአት የቆየ ወታደራዊ ህግ ያወጁት ዮን ሱክ የል ከጥር 15 2025 ጀምሮ በእስር ላይ ቆይተዋል።
በደቡብ ኮሪያ በስልጣን ላይ እያሉ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በቁጥጥር ስር በመዋልና በወንጀል በመከሰስ የመጀመሪያው የሆኑት ዮን ከእስር ቢፈቱም ባወጁት ወታደራዊ ህግ የቀረበባቸው ክስ መታየቱ ይቀጥላል ተብሏል።
የሀገሪቱ የህገመንግስታዊ ፍርድቤትም ዮን ወደ ስልጣናቸው ይመለሱ ወይስ ይባረሩ በሚለው ጉዳይ በቀጣይ ቀናት ውሳኔ እንደሚሰጥ ነው የተነገረው።
ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል በታህሳስ ወር መጀመሪያ ሀገሪቱ በወታደራዊ እዝ እንድትመራ ውሳኔ ሲያሳልፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሰሜን ኮርያ ጋር አደገኛ ሴራ እየሸረቡ ነው የሚል ምክንያት አቅርበው ነበር።
ወታደራዊ ህጉ እንደታወጀም ወታደሮች ከሄሊኮፕተሮች ወርደው፤ መስኮቶችን ሰባብረው ወደ ሀገሪቱ ፓርላማ ህንጻ ዘልቀው መግባታቸው የሚታወስ ነው።
ዴሞክራቲክ ፓርቲና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን ውንጀላው አይቀበሉትም።
ጦርነት በሌለበት የወታደራዊ ህግ የታወጀው የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ ለማስቆም በማለም ነው በሚል ፕሬዝዳንቱ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደጋጋሚ ስብሰባ መጥራታቸው አይዘነጋም።