የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ከሀገር እንዳይወጡ ታገዱ
ፓርቲያቸው "ፒፒፒ" ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል ስልጣናቸውን እስኪለቁ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱን እንዲመሩ ወስኗል

ፕሬዝዳንት ዮን ለስድስት ስአት በቆየው ወታደራዊ ህግ ምክንያት ከስልጣን እንዲለቁ ጫናው በርትቶባቸዋል
የደቡብ ኮሪያ የፍትህ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የል የውጭ ሀገራት ጉዞ እንዳያደርጉ አገደ።
ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት ውሳኔዋን ያሳለፈው የሀገሪቱ የሙስና ምርመራ ቢሮ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው።
ፕሬዝዳንት ዮን ባለፈው ሳምንት ሀገሪቱ በወታደራዊ እዝ እንድትመራ አዋጅ ማውጣታቸው ከስልጣናቸው ተነስተው በህግ ሊጠየቁ ይገባል የሚል ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል።
ወታደራዊ ህግ አዋጁ ከስድስት ስአታት በኋላ ቢሻርም ዮንን በምክርቤት ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ድምጽ እንዲሰጥባቸው ከማድረግ አላዳናቸውም።
ፓርቲያቸው "ፒፕል ፓወር ፓርቲ" በቅዳሜው የምክርቤት ድምጽ አሰጣጥ ራሱን በማግለል ከስልጣን መነሳት ቢታደጋቸውም የወንጀል ምርመራው ግን አልተቋረጠም።
ፕሬዝዳንቱ በ"ስነስርአት ስልጣን እስኪለቁ" ድረስም የፓርቲው መሪ ሀን ዶንግ ሆን እና የደቡብ ኮሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀን ዱክ ሶ ሀገሪቱን እንዲመሩ ከውሳኔ ላይ መደረሱን ፓርቲው አስታውቋል።
የፒፒፒ መሪ ሃን ዶንግ ሆን በትናንትናው እለት በሰጡት መግለጫ ፕሬዝዳንት ዮን ስልጣናቸውን እስከሚለቁ ድረስ የትኛውንም የውጭ ጉዞ አያደርጉም፤ ዲፕሎማሲያዊ እና ሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ላይም ስልጣን አይኖራቸውም ብለዋል።
ዋነኛው ተቃዋሚ ዴሞክራቲክ ፓርቲ በበኩሉ የገዥው ፓርቲን ውሳኔ "ህገወጥ፣ ኢህገመንግስታዊ እና ሁለተኛ መፈንቅለ መንግስት" ነው በሚል ተቃውሞታል።
የገዥው ፓርቲ መሪ መሰል ውሳኔዎችን እንዲያሳልፍ ስልጣን የሰጠው አካል የለም ሲል መቃወሙንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየሳምንቱ ቅዳሜ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልን ከስልጣን ለማንሳት ድምጽ እንደሚሰጡም ነው የገለጹት።
ደቡብ ኮሪያውያን በአሁኑ ወቅት ሀገራቸው በማን እየተመራች እንደሆነ ግራ እንደገባቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ግን ፕሬዝዳንት ዮን አሁንም ድረስ ጦሩን እንደሚያዙ አስታውቋል። ይህም ከሰሜን ኮሪያ ጸብ አጫሪ ድርጊት ቢፈጸም ዮን ውሳኔ እንደሚያሳልፉ ቢያመላክትም በርካቶች ጥርጣሬ አላቸው።
ከወታደራዊ ህግ አዋጅ በኋላ ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ የታዩት ፕሬዝዳንቱ ለተፈጠረው ትርምስና ውጥረት ይቅርታን ቢጠይቁም ተቃዋሚዎች ግን ከስልጣን ሊነሱ ይገባል በሚለው አቋማቸው ጸንተዋል።
በደቡብ ኮሪያ ፍትህ ሚኒስቴር ሌሎች የዮን አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣናትም የውጭ ሀገር ጉዞ እንዳያደርጉ አግዷል።