
የቦምብ ጥቃቱ ከሰሜን ኮሪያ በ25 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ቡቸን ከተማ ላይ ነው የተፈጸመው
በደቡብ ኮሪያ በልምምድ ላይ የነበረ የጦር ጄት በስህተት በንጹሃን የመኖሪያ መንደር ላይ ቦምብ መጣሉን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መቁሰላቸው ተገለጸ።
የደቡብ ኮሪያ አየር ኃይል በዛሬው እለት እንዳታወቀው ከሆነ፤ በልምምድ ላይ የነበረው የጦር ጄት በስህተት በንጹሃን መኖሪያ መንደር ላይ ስምንት ቦምቦችን ጥሏል።
አየር ኃይሉ በመግጫው ከኬ.ኤፍ 16 (KF-16) ተዋጊ ጄት የስልጠና ተልእኮ በማካሄድ ላይ እያለ ባልተለመደ ሁኔታ “Mk 82” የተባሉ ቦምቦች በመኖሪያ መንደር ላይ መጣሉን አረጋግጧል።
የአየር ድብደባው ከሰሜን ኮሪያ በ25 ሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቡቸን ከተማ ላይ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ እንደተፈጸመ ጦሩ አስታውቋል።
በስህተት በተፈጸመው የአየር ጥቃት በንጹሃን ላይ ጉዳት መድረሱን ያስታወቀው አየር ኃይሉ፤ ምን ያክል ሰው እንደተጎዳ እና የጉዳታቸው መጠን ምን ያክል ነው የሚለውን ግን ከመግለጽ ተቆጠቧል።
ከስፍራው የወጡ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርች እንደሚያሳዩት ከሆነ በአየር ጥቃቱ በ4 ሰዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስ በ3 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል።
የደቡብ ኮሪያ አየር ኃይል በደረሰው አደጋ ማዘኑን በመግለጽ፤ አደጋው በሰው ሰራሽ ስህተት አሊያም በቴክኒክ ችግር ነው የደረሰው የሚለውን ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
እንደ ዮንሃፕ ገለጻ የአየር ጥቃቱ የተፈጸመው ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር በቡቾን ባደረገችው የቀጥታ የተኩስ ወታደራዊ ልምምድ ላይ ነው።
በስህተት ንጹሃን ላይ የተተኮሰው ቦምብም “MK-82” የተባለ እና 227 ኪሎ ግም ክብደት ያለው ሲሆን፤ በውጊያ ወቅት የጠላት ኢላማዎችን በውስን ሁኔታ ውስጥ ለማጥቃት የሚያስችል ነው ተብሏል።