ደቡብ ኮሪያ ለጎረቤቷ ሙዚቃዎች፣ ዶላርና በራሪ ወረቀቶችን የያዙ ፊኛዎች ላከች
“ኪም ጆንግ ኡን ቆሻሻ በመላክ ሴኡልን ቢሳደብም እኛ ግን እውነትና ፍቅርን ልከናል” ብሏል በደቡብ ኮሪያ የሚገኝ አንቂ ቡድን
ፒዮንግያንግ በቅርቡ 15 ቶን የሚመዝኑ ቆሻሻዎችን በ3 ሺህ 500 ፊኛዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳ ይታወሳል
በደቡብ ኮሪያ የሚገኝ የማህበረሰብ አንቂ ቡድን ወደ ሰሜን ኮሪያ ሙዚቃዎች፣ ዶላርና በራሪ ወረቀቶችን የያዙ ፊኛዎችን መላኩን ገለጸ።
ለሰሜን ኮሪያ ነጻነት እታገላለሁ የሚለው ቡድን መሪ ፓርክ ሳንግ ሃግ እንዳስታወቀው፥ 200 ሺህ በራሪ ወረቀቶችን፣ 5 ሺህ የደቡብ ኮሪያ ኬ-ፖፕ ሙዚቃና ድራማዎች የተጫኑባቸው ፍላሾች እንዲሁም 2 ሺህ የ1 ዶላር ኖቶች በ10 ፊኛዎች ከድንበር ከተማዋ ፖቺዮን ወደ ሰሜን ኮሪያ ተልከዋል።
ፓርክ ሳንግ ሃግ ከሰሜን ኮሪያ ከድቶ የወጣውና በደቡብ ኮሪያ መኖር የጀመረው ከ24 አመት በፊት ነው።
የመሰረተው “የሰሜን ኮሪያ ነጻነት ታጋዮች” ቡድንም ከዚህ ቀደም በፊኛዎች ወደ ሰሜን ኮሪያ በራሪ ወረቀቶችን ሲልክ መቆየቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
በዛሬው እለት በፊኛዎች የተላኩት በራሪ ወረቀቶችም የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን የሚቃወሙ መልዕክቶች የተጻፉባቸው ናቸው ተብሏል።
ፒዮንግያንግ በቅርቡ 15 ቶን የሚመዝኑ ቆሻሻዎችን በ3 ሺህ 500 ፊኛዎች ወደ ደቡብ ኮሪያ መላኳ ይታወሳል።
በድንበር ከተማዎች ውጥረት የፈጠረው ክስተት ሴኡል ከፒዮንግያንግ ጋር በ2018 የደረሰችውን ወታደራዊ ስምምነት አቋርጣ በድንበር አካባቢ ወታደራዊ ልምምድ እንድትጀምር ማድረጉም አይዘነጋም።
እነፓርክ ሳንግ ሃግ ግን የኪም ጆንግ ኡን አስተዳደር ወደ ደቡብ ኮሪያ የላከው ቆሻሻ 50 ሚሊየን የሀገሪቱን ህዝብ ክብር የማይመጥን አሳፋሪ ድርጊት መሆኑን በመግለጽ አጻፋውን ከመመለስ ይልቅ “ለሰሜን ኮሪያውያን እውነትና ፍቅርን መላክን መርጠናል” ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ የልም ሰሜን ኮሪያ ጸብ አጫሪና አሳፋሪ ድርጊቷን ገፍታበታለች ሲሉ ወቅሰዋል።
ፕሬዝዳንቱ የኮሪያ ሰማዕታትን ለማሰብ በተዘጋጀ ስነስርአት ላይ “ከሰሜን ኮሪያ ጋር ሰላም ለማስፈን ሀይልን ማጠናከር ወሳኝ ነው” ማለታቸውን ተዘግቧል።
ሴኡል በድንበር ላይ የሚገኘውንና የሚረብሽ ድምጽ ማጉያ ከስድስት አመት በኋላ ስራ አስጀምራለሁ በሚል ማስጠንቀቋን ተከትሎ ፒዮንግያንግ የቆሻሻ ፊኛዎችን ወደ ጎረቤቷ መላኳን ማቋረጧ የሚታወስ ነው።
ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ኪም ጆንግ ኡንን የሚያጥላሉ በረሪ ወረቀቶች በፊኛዎች ከተላኩ ግን ቆሻሻ መላኳን እንደምትገፋበት ገልጻ ነበር።