“ጠላቶቻችን ከገፋፉን የኒዩክሌር ጥቃት ለመፈጸም አናመነታም” - ኪም ጆንግ ኡን
አሜሪካ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን በኮሪያ ልሳነ ምድር የጀመሩትን ወታደራዊ ልምምድ ተከትሎ ነው የሰሜን ኮሪያው መሪ ማስጠንቀቂያውን ያሰሙት
ፒዮንግያንግ ከቀናት በፊት የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ማድረጓ ይታወሳል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሀገራቸው የኒዩክሌር መሳሪያዎቿን መጠቀም ልትጀምር እንደምትችል አስጠንቅቀዋል።
ኪም “ጠላቶቻችን በኒዩክሌር መሳሪያዎች ጸብ ለማጫር ከሞከሩ እኛም የኒዩክሌር ጥቃት ለመፈጸም አናመነታም” ማለታቸውን የሀገሪቱ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ሰኞ ከአምስት ወራት በኋላ አህጉር አቋራጭ የባለስቲክ ሚሳኤል መሞከሯ ይታወሳል።
ኪም ጆንግ ኡን ሚሳኤሉን የሚሰሩ ባለሙያዎችን ጎብኝተው ሲያበረታቱ “ወታደራዊ ሃይላችን የትኛውም ሃይል ለሚፈጽመው ጥቃት አጻፋውን ለመመለስ ዝግጁ ነው” ብለዋል።
አሜሪካን መምታት ይችላል የተባለው የሃውሶንግ 18 ባለስቲክ ሚሳኤል መተኮስ የጸጥታው ምክር ቤትን እገዳ የተለላፈ ነው ያሉት አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በትናንትናው እለትም ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖቻቸው የተሳተፉበትን የጦር ልምምድ ከጃፓን ጋር ማካሄድ ጀምረዋል።
በኮሪያ ልሳነ ምድር በመካሄድ ላይ ያለውን ወታደራዊ ልምምድ እንደ ጦርነት ማስጀመሪያ ጸብ አጫሪ ድርጊት የምትመለከተው ፒዮንግያንግ ማስጠንቀቂያዋን አሰምታለች።
የኪሚ ጆንግ እህት ኪም ዮ ጆንግ በበኩላቸው የመንስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት የሰኞውን የባለስቲክ ሚሳኤል መተኮስ አስመልክቶ ያደረገው ስብሰባ የፒዮንግያንግን ራስን የመከላከል መብት ያላከበረ በሚል ተቃውመውታል።
“የጸጥታው ምክርቤት ሃላፊነት የጎደለው ድርጊት በሚፈጽሙትናን የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት በሚያባብሱት አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ላይ ሊያተኩር ይገባል” ሲሉ መናገራቸውንም ሬውተርስ ዘግቧል።
ዋሽንግተን ወደ ሴኡል ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፎችን ለመላክ መወሰኗም የኮሪያ ልሳነ ምድር ውጥረትን እንዳያባብሰው ተሰግቷል።