ደቡብ ኮሪያ በ2017 የሰሜን ኮሪያውን መሪና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችን የሚያጠፋ “ገዳይ ቡድን” ለማዋቀር ማቀዷን መግለጿ ይታወሳል
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያውን መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለመግደል ልምምድ ማድረጋቸው ተገለጸ።
ዋሽንግተን እና ሴኡል በመጋቢት ወር 2023 ከአምስት አመት በኋላ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በዚህ ወታደራዊ ልምምድ ላይም “አንገት ቀልቶ የመግደል ኦፕሬሽን” የተሰኘና ኪም ጆንግ ኡን ላይ ያነጣጠረ ልምምድ ተካቶበት ነበር ብሏል የብሪታንያው ጋዜጣ ዴይሊ ኤክስፕረስ።
ሴኡል ኪምን የመግደል ውጥኗን በይፋ ከስድስት አመት በፊት ይፋ ማድረጓንም ያወሳል ጋዜጣው።
የቀድሞው የደቡብ ኮሪያ የመከላከያ ሚኒስትር ሶንግ ያንግሞ በ2017 ድምጹን አጥፍቶ ኪም ጆንግ ኡን እና ሌሎች የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ መሪዎችን የሚያጠፋ “ገዳይ ቡድን” ለማዋቀር ማቀዷን ይፋ ማድረጋቸውንም ያስታውሳል።
ይህን እቅዷን ለማሳካትም ባለፈው ወር ከአሜሪካ ስፔሻል ፎርስ ጋር በመቀናጀት አዲስ “አንገት የመቅላት ልምምድ” ማድረጓን ሴኡል ማረጋገጧን ነው ዴይሊ ኤክስፕረስ ያስነበበው።
የአሜሪካው ዴይሊ ቢስት ድረገጽም ዋሽንግተን እና ሴኡል ልምምዱን ስለማድረጋቸው ዘግቧል።
የሰሜን ኮሪያን መሪዎች የሚገድል፣ የሚሳኤልና ኒዩክሌር ጣቢያዎችን የሚቆጣጠርና ጥቃት የሚፈጽም “ገዳይ ቡድን” የተለያዩ ልምምዶችን ማድረጉንም ነው የሚጠቅሰው።
ልምምዱ የተጠናቀቀው ሰውን እንዴት በፍጥነት አንገቱን ቆርጦ መግደል እንደሚቻል በመለማመድ መሆኑን በማንሳትም የሰሜን ኮሪያው መሪ እና ባለስልጣናቶቻቸውን እንዴት መግደል ይቻላል በሚለው ዙሪያ ከ2017 ጀምሮ የተጠነሰሰው የግድያ እቅድ መቀጠሉን የሚያረጋግጥ ዘገባን ይዞ ወጥቷል።
የቀድሞው የአሜሪካ ስፔሻል ፎርስ አባሉ ኮለኔል ዴቪድ ማክስዌል፥ “አንገት የመቅላት ግድያ ተልዕኮ የሚካሄደው ትልቅ ዋጋ ላለው ግለሰብ ነው፤ የአንድ ጦር ከፍተኛ መሪ (ኪም ጆንግ ኡን) ከተገደለ የእባቡ አናት እንደተቆረጠ ይቆጠራል” ይላሉ።
በርግጥ ዋሽንግተን እና ሴኡል ከልምምድ ባለፈ የግድያ ሙከራውን እስካሁን ስለማድረጋቸው ባይነገርም ኪም ጆንግ ኡን ልምምዱን እንደቀላል ይመለከቱታል ተብሎ አይጠበቅም።
ሴኡል የሰሜን ኮሪያውን መሪ ለመግደል ማሴሯን በይፋ በመከላከያ ሚኒስትሯ በ2017 ስትናገር ስድስተኛውን የኒዩክሌር ሙከራ ያደረጉት ኪም ጦራቸውን ለማይቀረው ጦርነት እንዲዘጋጅ አሳስበዋል።
“ሴኡል እንደጠላት ስለፈረጀችን በኮሪያ ልሳነ ምድር በየትኛውም ጊዜ ጦርነት ሊነሳ ይችላል” ያሉት ወጣቱ መሪ፥ የኒዩክሌርና ሚሳኤል ፕሮግራማቸው እንዲጠናከር በቅርቡ ማሳጠንቀቃቸውም አይዘነጋም።