ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ወታደራዊ ልምምዳቸውን እንደገና ሊጀምሩ ነው
ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ ከዚህ በፊት ሚሳኢል የማስወንጨፍ ልምምድ አድርገው ነበር
ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት በጋራ ባደረጉት ወታደራዊ ልምምድ ላይ 8 የባላስቲክ ሚሳኢሎችን ማስወንጨፋቸው ይታወሳል
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከዚህ በፊት ሲያደርጉት የነበረውን ወታደራዊ ልምምድ እንደገና ሊጀምሩ መሆኑን አስታወቁ፡፡
ሀገራቱ ከዚህ በፊት ወታደራዊ ልምምድ ሲያደረጉ የነበረ ቢሆንም መሃል ላይ ሳይካሄድ ቆይቶ ነበር፡፡ ከሰሜን ኮሪያ ጥቃት “ሊሰነዘር ይችላል” የሚል ስጋት የነበራቸው ደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ፣ ሚሳዔል የማስወንጨፍ ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ መስሪያ ቤት፤ ከአሜሪካ ጋር የሚከናወነው ወታደራዊ ልምምድ እንደሚጀመር አስታውቋል፡፡ የደቡብ ኮሪያ ጦር የመስክ ወታደራዊ ልምምዳቸውን በሚቀጥለው ወር እንደሚያደርጉም ነው መስሪያ ቤቱ የገለጸው፡፡
የሁለቱ ሀገራት ወታደሮች በሚቀጥለው ወር በሚጀምሩት ወታደራዊ ልምምድ 11 የመስክ ላይ ስራዎችን እንደሚያከናውኑ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ በዚህ ወታደራዊ ልምምድ የአየር ላይና የምድር ላይ የጦር ትርኢቶች እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ሀገሪቱ ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን ታሳቢ ያደረገ የሚሳኢል መከላከያ ስርዓቷን ማሳደግ እንደምትፈልግ ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባዩ ይህንን ያሉት ሰሜን ኮሪያ በዚህ ዓመት ብቻ ስድስት ጊዜ የሚሳኢል ሙከራ ማድረጓን ተከትሎ ነው ተብሏል፡፡ ፒዮኝግያንግ በዚህ ዓመት ብቻ ስድስት ጊዜ ሚሳኢል የሞከረች ሲሆን ሰባተኛውን በማንኛውም ሰዓት ልትሞክር እንደምትችል ተሰግቷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ ሚሳኢል ማስወንጨፏን ተከትሎ ስጋት የገባት አሜሪካ ሚያዚያ ላይ አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ ወደ ቀጠናው ማሰማራቷን መግለጿ ይታወሳል።አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ከለዚህ ቀደም በጋራ ባደረጉት ወታደራዊ ልምምድ ላይ 8 የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፋቸው ይታወሳል።