አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በጋራ በመሆን 8 የባላስቲክ ሚሳዔሎችን አስወነጨፉ
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ሚሳዔሎቹን ያስወነጨፉት ለሰሜን ኮሪያ ምላሽ ለመስጠት ነው
ሰሜን ኮሪያ በትናትናው እለት 8 ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏ ይታወሳል
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በዛሬው እለት በጋራ ባደረጉት ወታደራዊ ልምምድ ላይ 8 የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ማስወንጨፋቸው ተነግሯል።
ሀገራቱ በጋራ ያደረጉት የሚሳዔል ማስወንጨፍ ሙከራ ሰሜን ኮሪያ በትናትናው እለት ላካሄደችው የሚሳዔል ሙከራ ምላሽ መሆኑም ታውቋል።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ጥምር ጦር አዛዥ በሰጡት መግለጫ፤ በዛሬው እለት የተወነጨፉት ሚሳዔሎቹ “ታክቲካል ሚሳዔል ሲስተም” በመባል የሚታወቁ ሲሆን፤ በተለምዶ የጃፓን ባህር ተብሎ ወደሚጠራው የምስራቅ ባህር ነው የተወነጨፉት ብለዋል።
“ጦራችን ሰሜን ኮሪያ ዓለም አቀፍ ህጎችን በመጣስ የምታካሂዳቸው ተከታታይ የባላስቲክ ሚሳዔል ሙከራዎች ያወግዛል” ያሉት አዛዡ፤ ከዚህ ተግባሯ በአፋጥን እንድትቆጠብም አሳስበዋል።
ሰሜን ኮሪያ በትናትናው አለት ብቻ ስምንት የባላስቲክ ሚሳዔሎችን ወደ ምስራቅ የባህር ክልሏ ማስንጨፏ ይታወሳል።
ሚሳዔሎቹ ከምድር ከ25 እስከ 90 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ ከ110 እስከ 600 ኪሎ ሜትር ያክል ርቀት መብረራቸውም ተገልጿል።
ሰሜን ኮሪያ የባላቲክ ሚሳዔል ሙከራውን ያደረገችው አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በፊሊፒንስ ባህር ላይ ስያካሂዱ የነበሩትን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ማጠናቀቃቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተነግሯል።
የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ሰሜን ኮሪያ በሀገሪቱ ሰሜን ምስራቅ በምትገኘው ፑንጌይሪ ከተማ አቅራቢያ የኒውክሌር ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጀች እንደሆነ ምልክቶች ታይዋል ብለዋል።
ሰሜን ኮሪያ በያዝነው ዓመት የተገመተውን የኒውክሌር ሙከራ ካካሄደች ከፈረንጆቹ 2006 ወዲህ ብቻ ለ7ኛ ጊዜ እንደሚሆንም ይጠበቃል።