ደቡብ ኮሪያን በኒውክሌር ልትመታ እንደምትችል ሰሜን ኮሪያ አስጠነቀቀች
ሰሞነኛውን የሴዑል ባለስልጣናት መግለጫን ተከትሎ ነው ፒዮንግያንግ ማስጠንቀቂያውን የሰጠችው
በድንገት ልታጠቃት የምትሞክር ከሆነ የተመረጡ ዒላማዎችን እንደምታወድም ፒዮንግያንግ አስጠንቅቃለች
ደቡብ ኮሪያ ልታጠቃት የምትሞክር ከሆነ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿን እንደምትጠቀም ሰሜን ኮሪያ አሳሰበች፡፡
ጦርነትን አንፈልግም ያለችው የሃገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ ከሴዑል የሚቃጣ የትኛውም ዐይነት ድንገተኛ ጥቃት ካለ የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቻችንን እንጠቀማለን ስትል ተናግራለች፡፡
ኪም ዮ ጆንግ ከወሳኝ የሃገሪቱ ባለስልጣናት መካከል ነች፡፡
ይህን የተናገረችው የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስትር ባሳለፍነው አርብ ሰሜን ኮሪያን ለማጥቃት የሚችል አቅም እንዳላቸው መናገራቸውን ተከትሎ ነው፡፡
ጆንግ ንግግሩን ትልቅ ስህተት ብላዋለች፡፡
መከላከያ ሚኒስትሩ ሹህ ዉክ ጦራችን በሰሜን ኮሪያ የትኛውንም ዒላማ በብቃትና በፍጥነት ለማደባየት የሚችል አቅም አለው፤ በተለያዩ ርቀቶች የሚምዘገዘጉ ሚሳዔሎችም አሉን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ይህ ንግግር ጎረቤት ሃገር ሰሜን ኮሪያን አላስደሰተም፡፡ ጸብ አጫሪ በሚልም መሪውን ኪም ጆንግ ኡንን ጨምሮ ሌሎች የፒዮንግያንግ ባለስልጣናት ንግግሩን አውግዘዋል፡፡
ሴዑል ቀድሞ ለማጥቃት የምታደርገው ሙከራ ካለ ዋና ዒላማዎችን እንደሚያወድሙም ነው የዛቱት፡፡
የኪም ጆንግ ኡን ማሳሰቢያ አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል አደረጉት ለተባለው ንግግር የተሰጠ ምላሽ እንደሆነም ነው የተነገረው፡፡
ሙን ጃኤ ኢንን ተክተው ደቡብ ኮሪያን በፕሬዝዳንትነት መምራት የጀመሩት ዩን ሱክ የሰሜን ኮሪያን ስጋቶች መቋቋም የሚችልና የፈረጠመ አቅም ያለው ጦር ሰራዊት እንዲገነባ ጥሪ ስለማቅረባቸው ተነግሯል፡፡
አስፈሪ ወታደራዊ አቅምን መገንባቷን እንደምትቀጥል ያስታወቀችው ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ “አውሬው” ያለችውን ተምዘግዛጊ ሚሳዔል ይፋ ማድረጓ የሚታወስ ነው፡፡