ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችው ሚሳይል አየር ላይ መፈንዳቱ ተገለጸ
የደቡብ ኮሪያ ጦር አዛዥ እንደተናገሩት ሚሳይሉ የተተኮሰው ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በቅርብ ርቀት ከሚገኝ ቦታ ነው
የደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና ጃፓን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራው በርካታ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ህጎችን ይጥሳል በሚል አውግዘውታል
ሰሜን ኮሪያ ከምስራቅ ጠረፍ ያስወነጨፈችው ሀይፐርሶኒክ ሚሳይል እንደሆነ የተገመተው መሳሪያ አየር ላይ መፈንዳቱን የደቡብ ኮሪያ ጦር አስታውቋል።
የደቡብ ኮሪያ ጦር አዛዥ እንደተናገሩት ሚሳይሉ የተተኮሰው ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ በቅርብ ርቀት ከሚገኝ ቦታ ነው።
የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ሚሳይሉ በ100 ኪሎሜትር ከፍታ ላይ ሲበር እንደነበር እና 200 ኪሎሜትር ርቀት እንደሚሸፍን ገልጿል።
የደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ እና ጃፓን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራው በርካታ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ህጎችን ይጥሳል በሚል አውግዘውታል።
የደቡብ ኮሪያ እና አሜሪካ አየር ኃይሎች በኤፍ-22 እና ኤፍ-35 የጦር አውሮፕላኖች የታገዘ አመታዊ የጋራ ልምምድ ማድረጋቸውንም ገልጸዋል።
የደቡብ ኮሪያ ባህር ኃይል ደቡብ ኮሪያን ከሰሜን ኮሪያ ጋር በሚያዋስነው የማሪታይም ድንበር በተናጠል ልምምድ አድርገዋል። ይህ ልምምድ የተካሄደው ሴኡል የኢንተር ኮሪያ ወታራዊ ስምምነትን ከሰረዘች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው።
የአሜሪካ፣ የኢንዶ ፓሲፊክ እዝ የሰሜን ኮሪያን ድርጊት አውግዞ፣ ፒዮንግያንግ ከእንዲህ አይነት ህጋዊ ያልሆነ እና ሰላም የሚያደፈርስ ተግባሯ እንድትቆጠብ ጥሪ አቅርቧል።
"ይህ ክስተት በአሜሪካ ወታደሮች፣ ግዛት እና አጋሮቿ ላይ ጥቃት ባያደርስም፣ ሁኔታውን መከታተላችንን እንቀጥላለን" ብሏል እዙ ባወጣው መግለጫ።
ሰሜን ኮሪያ ለመጨረሻ ጊዜ ሚሳይል የሞከረችው በፈረንጆች ባለፈው ግንቦት 30 ነበር።
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለምታደርገው ልምምድ የጦር ጄት ተሸካሚ መርከብ መላኳን ባለፈው ሳምንት የተቃወመችው ሰሜን ኮሪያ በርካታ የማስጠንቀቂያ ሙከራዎችን እንደምታደርግ አስጠንቅቃ ነበር።
የሚሳይል ማስወንጨፍ ሙከራው የተደረገው የኮሪያ የእርስበእርስ ጦርነት የተጀመረበት 74ኛ አመት ከተከበረ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ባለፈው ሳምንት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ወታደራዊ ጥቃት በሚሰነዘርባቸው ወቅት አንደኛቸው ለሌላኛቸው ሀሉንም አይነት ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሴኡል፣ ዋሽንግተን እና ቶኪዮ የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ግንኙት መጠናከር ያወገዙ ሲሆን የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ዩኦል ደግሞ ስምምነት "ኃላቀር" ሲሉ አጣጥተውታል።