ምዕራባውያን የተመድን ማዕቀብ ችላ በማለት ኑክሌር እና ባለስቲክ ሚሳይል ያበለጸገችውን ሰሜን ኮሪያን እንደ ስጋት ይቆጥሯታል
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ሩሲያ ሰሜን ኮሪያን ልታስታጥቅ እንደምትችል በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ፑቲን ይህን ያሉት ኑክሌር የታጠቀችውን ሰሜን ኮሪያን ከጎበኙ እና ከመሪው ኪም ጋር ወታራዊ ስምምነት ከተፈራረሙ ከአንድ ቀን በኋላ በቬትናም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ነው።
ምዕራባውያን የተመድን ማዕቀብ ችላ በማለት ኑክሌር እና ባለስቲክ ሚሳይል ያበለጸገችውን ሰሜን ኮሪያን እንደ ስጋት ይቆጥሯታል፤ የሞስኮ እና ፒዮንግያንግ ግንኙነትም ያሳስባቸዋል።
ፑቲን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ምዕራባውያን ዩክሬይንን እያስታጠቁ በመሆናቸው እና በሰጧት መሳሪያ ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን ስለፈቀዱ ሩሲያም ለምዕራባውያን ጠላት ለሆኑ ሀገራት በምላሹ እንደምታስታጥቅ ተናግረው ነበር።
ፑቲን በትናንትናው አስተያየታቸው ሩሲያ ከምታስታጥቃቸው ሀገራት ሰሜን ኮሪያ አንዷ ልትሆን ትችላለች ብለዋል።
ፑቲን "ፒዮንግያንግን ጨምሮ ለሌላው የአለም ክፍል መሳሪያ የማቅረብ መብት አለን። ከሰሜን ኮሪያ ጋር ስምምነት ስለደረስን ልናስታጥቃት እንችላለንን" ሲሉ ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ እና ሩሲያ ከሁለቱ በአንጀኛቸው ላይ ወታደራዊ ጥቃት በሚደርስበት ጊዜ ሌላኛቸው ሁሉንም አይነት ወታራዊ ድጋፍ ወዲያውኑ ለመስጠት የሚያስቸል ስምምነት ፑቲን እና ኪም ባለፈው ረቡዕ ተፈራርመዋል።
ፑቲን እንደሚገልጹት ከሆነ ይህ ስምምነት ምዕራባውያን ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ለማድረግ እንጂ የሰሜን ኮሪያን ወታሮች በዩክሬን ለማሳተፍ አይደለም።
ሰሜን ኮሪያ፣ ሩሲያ በዩክሬን ለምታካሂደው ወታራዊ ዘመቻ ሙሉ ድጋፍ ሰጥታለች፤ ፑቲንም ሰሜን ኮሪያ ላሳየችው ድጋፍ ምስጋና ችረዋታል።
አሜሪካ እና ዩክሬን፣ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን በምታካሄደው ጦርነት ጥቅም የሚውሉ የከባድ መሳሪያ ተተኳሽ እና ባለስቲክ ሚሳይሎችን ሰጥታለች ሲሉ ይወነጅላሉ።
ሰሜን ኮሪያ ግን ሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ነው ስትል ውንጀላውን በተደጋጋሚ አጣጥላለች።
ሩሲያ በፈረንጆች የካቲት 2022 በዩክሬን ልዩ ያለችውን ወታራዊ ዘመቻ ከጀመረች ወዲህ ሰሜን ኮሪያን ጨምሮ ከምዕራባውያን ጋር ቅራኔ ውስጥ ከገቡ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን በማጠናከር ላይ ነች።