ባንኩ የገንዘብ ድጋፉን ያደረገው ለኢትዮጵያ፣ኬንያ እና ሶማሊያ ነው
የዓለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለሶስት ሀገራት 385 ሚሊዮን ዶላር መደበ፡፡
በዚህ ዓመት በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ ያልታየ እንደሆነ የዓለም ምግብ ድርጅት ፋኦ ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወሳል።ይህ ድርቅ በሶማሊያ ስድስት አካባቢዎች ባስከተለው ጉዳት ረሀብ ተከስቷል ተብሏል።
የዓለም ባንክም በድርቅ ለተጎዳው የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት 385 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ኬንያ እና ሶማሊያ ደግሞ በዓለም ባንክ ድጋፉን ከሚያገኙት ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው ሲል ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ለአራት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ያልዘነበ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ለከፋ ጉዳት ሊዳረጉ ችለዋል።
ድርቁ ከሰዎች ጉዳት ባለፈም ከሶስት ሚሊዮን በላይ የቤት እንስሳት የሞቱ ሲሆን ይህም በተለይም የምግብ ደህንነትን የከፋ እንዲሆን አድርጎታልም ተብሏል።
ላለፉት 40 ዓመታት ያልታየ ድርቅ በአፍሪካ ቀንድ እንደተከሰተ የተገለጸው ይህ ድርቅ በሶማሊያ 6 ሚሊዮን በኬንያ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን እንዲሁም በኢትዮጵያ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።