ሰሜን ኮሪያ ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ የቀረበላትን የድጋፍ ጥያቄ ውድቅ አደረገች
ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሐ ግብሯ በየትኛውም ዐይነት ድጋፍ የሚቋረጥ እንዳልሆነ አስታውቃለች
ድጋፉ በአዲሱ የደቡብ ኮሪያ መሪ የቀረበ ነበረ
በድጋፍ ምክንያት ለማቋረጥ የጀመረችው የኒውክሌር መርሐ ግብር እንደሌለ ሰሜን ኮሪያ አስታወቀች።
ፒዮንግያንግ ከጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ የቀረበላትን የድጋፍ ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።ጥያቄው ውድቅ የተደረገው በሃገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ዑን እህት ኪም ዮ ጆንግ ነው።
የድጋፍ ጥያቄው በአዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮል የቀረበ ነበረ።
ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈ ንግግራቸው ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር እና የሚሳኤል መርሐ ግብሯን የምታቋርጥ ከሆነ ምጣኔ ሃብታዊዉን ጨምሮ ሌሎች ዘርፈብዙ ድጋፎች እንደሚደረጉላት ተናግረዋል። ሆኖም ይህ ፒዮንግያንግን አስቆጥቷል።
- አሜሪካ፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የጋር የባልስቲክ ሚሳኤል ልምምድ ማድረጋቸውን ገለጹ
- ሩሲያ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ልታጠናክር እንደምትችል ገለጸች
ንግግሩን ክፉኛ የተቹት ኪም ዮ ጆንግም 'የደንቆሮ ለቅሶ መልሶ መልሶ' በሚል ሃገራቸው እንዲህ ዐይነት ጥያቄዎችን በምንም ዐይነት መንገድ እንደማትቀበል ደጋግማ ማስታወቋን ተናግረዋል።
የፒዮንግያንግ የኒውክሌር መርሐ ግብር በየትኛውም ዐይነት ድጋፍ የሚቋጥ እንዳልሆነም ነው የተናገሩት።
"ለበቆሎ ኬክ ሲል እጣ ፋንታውን የሚቀይር ማንም የለም" ሲሉም ተናግረዋል፤ ሃገራቸው መርሐ ግብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል በመጠቆም።
ከአሜሪካ ጋር የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የምታደርገው ደቡብ ኮሪያ ለሃገራቱ ግንኙነት መሻሻል አለኝ የምትለውን ዝግጁነትም አጠይቀዋል።
ፒዮንግያንግ ከሰሞኑ ያስወነጨፈቻቸውን ሚሳኤሎች ከየት እንደተወነጨፉ በደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ መሪዎች የተሰጠውን መረጃ በማጣቀስም በሃገሪቱ መከላከያ አቅም ስላቅ የሚመስል አስተያየትን ሰጥተዋል ዮ ጆንግ።
ይህም የሴዑል ባለስልጣናትን አስቆጥቷል እንደ ኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ።
የሃገሪቱን የግንኙነት ጉዳዮች የሚከታተሉት የደቡብ ኮሪያ የውህደት ሚኒስትርም ንግግሩን አሳፋሪ ሲሉ ተችተዋል።