ደቡብ ሱዳን ከሁለት ወራት በኋላ ልታደርገው የነበረውን ምርጫ በሁለት አመት አራዘመች
ሀገሪቱ የምትገኝበት ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ አመቺ አይደለም ተብሏል
በተደጋጋሚ እየተራዘመ የሚገኘው ምርጫ ዳግም ግጭትን እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት አለ
ደቡብ ሱዳን ለረጅም ጊዜ ሲራዘም የቆየውን ምርጫ ለተጨማሪ ሁለት አመት አራዘመች፡፡
ከሱዳን ከተገነጠለች በኋላ በአስከፊ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ለአምስት አመታት የሰነበተችው ሀገር ከ2018 ወዲህ በአንጻራዊ ሰላም ውስጥ ትገኛለች፡፡
በ2020 የተቋቋመው የሽግግር መንግስት ምርጫ ሲያራዝም ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር እና ተቀናቃኛቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሪክ ማቻር የ40 ሺህ ሰዎችን ህይወት የነጠቀውን ግጭት ለማቆም የሰላም ስምምነት ከፈጸሙ በኋላ በሽግግር መንግስት ውስጥ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን በተደጋጋሚ እየተራዘመ የሚገኝው ምርጫ በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል ዳግም ግጭትን እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት አለ፡፡
በሽግግር ውስጥ የምትገኘው ጁባ አዲስ አስተዳዳር ለመመስረት ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅቶችን ስታደርግ የቆየች ቢሆንም ወቅታዊ ሁኔታዎች ለምርጫ አመቺ አይደሉም ብላለች፡፡
ምርጫው መራዘሙን ይፋ ያደረጉት የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማርዲያት በታህሳስ ወር ይደረጋል ተብሎ የነበረው ምርጫ ለ2026 ተራዝሟል ነው ያሉት፡፡
ቋሚ ህገ መንግስት ማርቀቅ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ፣ የምርጫ መሰረተ ልማቶችን ማሟላት እና ሌሎችም ቅድመ ሁኔታዎች በበቂ ሁኔታ ባለመሟላታቸው ምርጫው እንዲራዘም ምክንያት መሆኑ ነው የተነገረው፡፡
የፕሬዝደንቱ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ቱት ጋትሉዋክ ጊዜው የተራዘመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ከጸጥታ እና የምርጫ ቦርድ ተቋማት በቀረበ ሀሳብ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የምርጫው መራዘም አስፈላጊውን ሂደት እንድናሟላ እና የአምስት አመቱ የእርስ በእርስ ግጭት እንዳይደገም የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ባሳለፍነው ወር የደቡብ ሱዳን የምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ፕሮፌሰር አብዲንጎ አኮክ ሀገሪቷ ከምርጫ ሰሌዳ በእጅጉ ወደ ኋላ መቅረቷን ተናግረው የአለም አቀፍ መስፈርትን የማያሟላ ምርጫ ማድረግ ጥቅም አይኖረውም ነው ያሉት፡፡
ሀላፊው ባሳለፍነው ሰኔ የመርጮች ምዝገባ መደረግ ቢኖርበትም እስካሁን አለመደረጉ እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ግብአቶችን ለማሟላት የሚያስፈልጉ የገነዘብ ድጋፎች እጥረት እንዳጋጠማቸወም ገልጸዋል፡፡
በጎረቤት ሱዳን በተፈጠረው ግጭት በነዳጅ ማስተላለፍያ መስመሮቿ ላይ ጉዳት የደረሰባት ጁባ በከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ውስጥ የምትገኝ ሲሆን የመንግስት ሰራተኞችም ደመወዝ ከተከፈላቸው አንድ አመት ተቆጥሯል፡፡
በኢኮኖሚ ጫና እና በአየር ንብረት ለውጥ የተነሳ 9 ሚሊየን ወይም 73 በመቶ ህዝቧ የሰብአዊ ድጋፍ ላይ ህይወቱን መስርቷል፡፡