የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ በጦርነት ስትታመስ ወደ ቆየችው ደቡብ ሱዳን ገቡ
ደቡብ ሱዳን በዓለማችን ሶስተኛዋ ከፍተኛ የተፈናቃዮች ቀውስ ያለባት ሀገር ናት
ደብብ ሱዳናውያን የአባ ፍራንሲስ ጉብኝት “ፈተና ለበዛባት ሀገር አዲስ ምእራፍ እንዲሆን” እየጸለዩ ነው
የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ ለበርካታ አመታት በጦርነት ስትታመስ ወደ ቆየችው ደቡብ ሱዳን ገብተዋል፡፡
ይህ ታሪካዊ ነው የተባለለት ጉዞ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የረዥም ጊዜ ምኞት የነበረ ነው ተብሏል፡፡
አባ ፍራነስስ ገና ከሮም ወደ አፍሪካ ለማቅናት ሲያስቡ "አመታት በፈጀው ጦርነት ስትታመስ የቆየችው ደቡብ ሱዳን ብዙ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ እና በታላቅ ችግር ውስጥ እንዲኖሩ የሚያስገድደውን የማያቋርጥ ግጭት እንዲያበቃ ትናፍቃለች" ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡
የሮማው ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ያሉት በደቡብ ሱዳን ውስጥ አብዛኛው የህዝብ ቁጥር ያላቸውን ሶስት የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ከሚወክሉ እንደ የአንግሊካን ቁርባን መሪው ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ እና የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ጉባኤ አወያይ ሊቀ ጳጳስ ቄስ ኢየን ግሪንሺልድስ ጋር በመሆን ነው፡፡
ደቡብ ሱዳን በዓለማችን ሶስተኛዋ ከፍተኛ የተፈናቃዮች ቀውስ ያለባት ሀገር ናት፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ሀገሪቱን ለቀው ተሰደዋል ወይም በደቡብ ሱዳን ውስጥ ተፈናቅለዋል፣ ከእነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ህጻናት ናቸው።
ደቡብ ሱዳን እንደፈረንጆቹ በ2011 ነጻነቷ ብትቀዳጅም ፤ ከሁለት አመታት በኋላ በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ምክትላቸው ሪክ ማቻር ጋር በተፈጠረው ግጭት ለአመታት ወደ ማያባራ ቀውስ ገብታ መቆየቷ ይታወቃል፡፡
ያም ሆኖ አሁን ላይ በደቡብ ሱዳን ፖለቲኞች መካከል በ2018 በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የሀገሪቱ ፖለቲከኞች የሽግግር መንግስት ማቋቋም መቻላቸውና በ2024 ምርጫ ለማድረግ ከስምምነት መድረሳቸው በሀገሪቱ የነበረውን ግጭት እንዲያበቃ ተስፋ ሰጪ እርምጃ እንደሆነ ይወሰዳል፡፡
የወቅቱ የሮማው ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት አባ ፍራንሲስ የሶስት ቀናት የጁባ ጉብኝትም በሀገሪቱ ሰላም እንዲመጣ ከሀገሬው ሰዎች ጋር በመሆን ለፈጣሪያቸው የሚለምኑበት ትልቅ አጋጣሚ እንደሚሆን እየተገለጸ ነው፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያንም የአባ ፍራሲስ መምጣት “እጅግ እየተፈተነች ላለችው ሀገር አዲስ ምዕራፍ እንዲሆን” ተስፋ በማድረግ በመጸላይ ላይ ናቸው፡፡
አባ ፍራነስስ እንደፈረንጆቹ በ2019 ደቡብ ሱዳን በጎበኙበት ወቅት በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪክ ማቻር እግር ተንበርክከው እየሳሙ ደም አፋሳሹ ጦርነት እንዲያበቃ የለመኑበትና በርካቶችን ያስደነገጠ አጋጣሚ አይዘነጋም፡፡
የአባ ፍራንሲስ ልማናና ተማጽኖ ግጭቱን ሙሉ በሙሉ አስቁሞታል ባይባልም የሀገሪቱ ፖለቲኞች ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደረገ ነበር፡፡