የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ከ2 ሚሊየን በላይ ዜጎች እንዲመለሱ አሳሰቡ
ፕሬዝድንቱ ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ደቡብ ሱዳናዊያን ጥበቃ አደርጋለሁ ብለዋል
በኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናዊያን በስደተኝነት ተጠልለዋል
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ወደ ጎረቤት ሀገራት የተሰደዱ ዜጎች እንዲመለሱ አሳሰቡ።
ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ካገኘች ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ እርስ በርስ ጦርነት መግባቷ ይታወሳል።
- ደቡብ ሱዳን ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ዜጎችን ማሰር የሚፈቅደውን ህግ ልትሰርዝ ነው
በፕሬዝዳንት ሳልቫኬር ማያርዲት እና ምክትላቸው ሪክ ማቻር አለመስማማት ምክንያት ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገቡት ደቡብ ሱዳናዊያን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተሰደዋል።
ሀገሪቱ ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ እያደረገች ባለው የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ሶሞቱ ሚሊዮኖች ደግሞ ሀገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል።
ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት ያላት ደቡብ ሱዳን ዜጎቿ በጦርነቱ ምክንያት ወደ ጎረቤት ሀገራት እንደተሰደዱ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኪር በጎረቤት ሀገራት ተጠልለው ያሉ ደቡብ ሱዳናዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል ተብሏል።
በኢትዮጵያ ፣ ኬንያ እና ኡጋንዳ ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናዊያን በስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች እንዳሉ ቪኦኤ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ወደ ሀገራቸው ለሚመለሱ ደቡብ ሱዳናዊያን ድጋፍ እና ከለላ እንሰጣለን ብለዋል።
ደቡብ ሱዳን ከእናት ሀገሯ ሱዳን በፈረንጆቹ 2011 ላይ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ሉዓላዊ ሀገር መሆኗ ይታወሳል።