ደቡብ ሱዳን የሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላከች
ለዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ደቡብ ሱዳን ሰላም አስከባሪ ጦር ወደ ኮንጎ የላከች ቀዳሚ ሀገር ሆናለች
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ወታደሮቻቸውን ስነ-ምግባር እንዲጠብቁ እና ከወንጀል ድርጊቶች እንዲርቁ አሳስበዋል
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በጎረቤት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚሰማሩትን ከ700 በላይ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ሸኝተዋል።
ሳልቫ ኪር ወታደሮቹ በተልዕኮው እንዲጸኑ፣ ስነ-ምግባር እንዲጠብቁ እና ከወንጀል ድርጊቶች እንዲርቁ ማሳሰባቸውን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ወተደሮቻውን "ስነ-ምግባር እንድትጠብቁ እፈልጋለሁ፤ ወደ ሌላ ሀገር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሄደው ችግር የሚፈጥሩ ኃይሎች አሉ፤ ሴቶችንና ልጃገረዶችን ይደፍራሉ፤ እናንተ አታድርጉ” ብለዋል።
“ከሰላማዊ ሰዎች ምንም ነገር አትውሰዱ፤ በምትኩ የዜጎችን ህይወት ከአደጋ ጠብቁ” ሲሉ ፕሬዝዳንት ኪር በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ለሚገኘው የቀጣናው ኃይል ተናግረዋል።
ደቡብ ሱዳን በኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኘውን ኤም-23 አማጺን ለመዋጋት በምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ክልላዊ ኃይል የተመደበውን ከ700 በላይ “ጠንካራ ኃይሎችን” የያዘ ወታደራዊ ቡድን ልካለች።
በተልዕኮው የሀገሪቱን መልካም ገጽታ ለማምጣት ለሰላም አስከባሪ ኃይሉ ስርዓት እንዲያሰፍን ፕሬዝዳንት ኪር ጠይቀዋል።
የሀገሪቱ የመከላከያ እና የአርበኞች ጉዳይ ሚንስትር አንጀሊና ቴኒ ሀገሪቱ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለዓለም አቀፍ ሰላም የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት የቀጣናው ሰላም አስከባሪ ኃይል አባል በመሆኗ ኩራት ይሰማታል ብለዋል።
ኃይሉ ወዲያውኑ ወደ ኮንጎ እንደሚላክና በጎማ እንደሚሰፍር ተገልጿል።
ደቡብ ሱዳን እስካሁን ሰላም አስከባሪ ኃይሏን ወደ ኮንጎ የላከች ብቸኛዋ አገር ነች ተብሏል።
ከመጋቢት መጨረሻ ጀምሮ ኤም-23 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሰሜን መስራቅ ክፍል ጥቃቱን ማጠናከሩ ተነግሯል።