ጠንካራ የመከላከል አቅም የገነባው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን በግማሽ ፍጻሜው ለስፔን ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል
ምሽት ላይ በተደረጉ የአውሮፓ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ስፔን እና ፈረንሳይ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ስፔኖች ያለምንም ሽፈት ግስጋሴያቸውን ቀጥለዋል፡፡
ከአዘጋጇ ሀገር ጀርመን ጋር ትላንት ባደረጉት ጨዋታ 2ለ1 በሆነ ውጤት ያሸነፉት ስፔኖች ለዋንጫው የሚኖራቸውን ከፍተኛ ተፎካካሪነት በምሽቱ ጨዋታ በግልጽ አሳይተዋል፡፡
በሁለቱ ቡድኖች መካከል ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት ፍጹም የጨዋታ ፉክክር በታየበት ግጥሚያ በፔድሪ ተቀይሮ የገባው ዳኒ አልሞ በ51ኛው ደቂቃ ስፔንን መሪ ያደረገች ጎል ያስቆጠረ ሲሆን፥ ፍሎሪያን ዊርዝ በ89ኛው ደቂቃ ጀርመንን አቻ አድርጓል።
ጨዋታው ወደ ጭማሪ ስአት አምርቶ ሚኬል ሜሪኖ ለስፔን ወሳኝ ጎል አስቆጥሮ ሀገሩን ወደ ግማሽ ፍጻሜው በማሳለፍ ውለታን ውሏል።
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አማካይ ቶኒ ክሩስ በእግርኳስ ህይወቱ ለብሔራዊ ቡድኑ ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታው ሆኗል።
የአውሮፓ ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ምሽት 4 ስአት ሲቀጥል በሀምቡርግ ከተማ ፈረንሳይን ከፖርቹጋል ጋር አገናኝቷል።
ሁለት በራስ ላይ በተቆጠረ ግብ እና በአንድ ፍጹም ቅጣት ምት ሩብ ፍጻሜ መድረስ የቻለው ተከላካዩ የዲዴር ዴሾ ቡድን ትላንትም የግብ ክልሉን በፖርቹጋል ተጫዋቾች ላለማስደፈር አጥር ሰርቶ ተጫውቷል፡፡
በመደበኛው እና በጭማሪ ሰአት ግብ ያልተቆጠረበት የፖርቹጋል እና ፈረንሳይ ጨዋታ ወደ መለያ ምት አምርቶ 5ለ3 በሆነ ውጤት ፈረንሳይ ግማሽ ፍጻሜውን መቀላቀል የቻለችበት ውጤት ተመዝግቧል፡፡
የምሽቱን ጨዋታ ተከትሎ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ፔፔ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚያደርጉት የመጨረሻ ጨዋታ እንደሆነ ተነግሮ ነበር፡፡
ንጋት ላይ የብሄራዊ ቡድኑን አሰልጣኝ ጠቅሰው የወጡ መረጃዎች ደግሞ የተጨዋቾቹ እጣ ፈንታ አለመወሰኑን አመላክተዋል፡፡ አሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ የክርስቲያኖ እና ፔፔ በብሄራዊ ቡድኑ የሚኖራቸው ቆይታ ገና አልተወሰነም ብለዋል፡፡
ሮናልዶ በውድድሩ ከየትኛውም ተጫዋች የበለጠ የጎል ሙከራዎችን ቢያደርግም ግብ ማስቆጠር ተስኖት ከውድደሩ ውጭ ሲሆን ፔፔ በአውሮፓ ዋንጫ የተሳተፈ በእድሜ ትልቁ ተጫዋች ሪከርድን ይዟል፡፡
የሩብ ፍጻሜ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን ምሽት 1 ሰአት ላይ ኔዘርላንድ ከቱርክ ምሽት 4 ሰአት ላይ ደግሞ እንግሊዝ ከሲውዲን ጋር ይጫወታሉ፤ የሁለቱ ጨዋታ አሸናፊዎች ወደ ዋንጫ ለማለፍ የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
ትላንት በተደረጉ ጨዋታዎች ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀሉት ስፔን እና ፈረንሳይ በመጭው ማክሰኞ ፍልሚያቸውን የሚያደርጉ ሲሆን በማጥቃት ላይ ተመስርቶ ለሚጫወተው የስፔን ብሄራዊ ቡድን አጥር ሰርተው የሚከላከሉት ፈረንሳዮች ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡