ወንድሟን ለመሞሸር 12 ዓመታትን ተግታ ገንዘብ የቆጠበችው ቻይናዊ
ወንድ ልጅ የሚጠየቀው ጥሎሽ እየጨመረ መምጣት ቻይናውያንን ወደ ጎረቤት ሀገራት እንዲያማትሩ አድርጓቸዋል
ለታናሿ ቤትና መኪና ገዝታ ጥሎሽ እንዳያሳስበው ያደረገችው የ33 አመት ወጣት ውደሳም ወቀሳም እየቀረበባት ነው
የ33 አመቷ ቻይናዊ የወንድሟን ህይወት የተቃና ለማድረግ ድፍን 12 አመታትን ለፍታለች።
ታናሽ ወንድሟ አግብቶ ጎጆ ይቀልስ ዘንድም በርትታ ቆጥባለች። የራሷን ነገ በይደር አቆይታ ለወንድሟ መታተሯ ትዳር ይመሰርት ዘንድ ሃብት ልታስይዘው ነው።
ስሟ ያልተጠቀሰው የምስራቃዊ ቻይና አንሁይ ግዛት ነዋሪ ‘’ወንድሜን ለመዳር ያለፉትን 12 አመታት እየተቸገርኩም ቢሆን መቆጠብ ነበረብኝ’’ የሚል ሀሳቧን ሚያወን ለተሰኘ መገናኛ ብዙሃን ከሰጠች በኋላ የቻይናውያን መነጋገሪያ ሆናለች።
በቻይና እየጨመረ የመጣውን የሰርግ ወጪ ተግተን ካልቆጠብን ቆሞ የሚያስቀር ነው የምትለው ወጣት ኬክ እየጋገረች የምትሸጥበት አነስተኛ ምግብ ቤት አላት።
በቻይና ለሙሽሪት ቤተሰቦች የሚሰጠው ጥሎሽ ያሳሰባት እንስት የኔ የትዳር ፍላጎት ከታናሽ ወንድሜ በኋላ ይደርሳል ብላ ስትቆጥብ ከርማለች።
ድካሟም ፍሬ አፍርቶ 130 ካሬ ላይ ያረፈ ቤት እና መኪና ገዝታለታለች፤ የምትሰራበትን ምግብ ቤትም በስጦታ አበርክታለታለች።
ለራሴ ቤትም ሆነ መኪና መግዛት አላስብኩም የምትለው ወጣት ለ12 አመታት ለወንድሟ ጥሎሽ የሚሆን ገቢን ስትቆጥብ ለራሷ አዲስ ልብስ ለመግዛት እንኳን ትሳቀቅ እንደነበር ተናግራለች።
አንቺስ መች ለማግባት አሰብሽ ተብላ ስትጠየቅም “አሁን ጊዜው አይደለም፤ ወንድሜን መጀመሪያ ልዳር’” የሚል መልስ ሰጥታለች።
የጥሎሽ ነገር ሲነሳ እንደ ቻይናውያን ሙሽሮች ብሶት የሚሰማው አይገኝም።
የሙሽሪትን እጅ ይዞ ለመውጣት የሚጠየቀው ጥሎሽ ከአመት አመት እየጨመረ መምጣትም በርካቶች ትዳርን እንዲርቁ አንዱ ግፊ ምክንያት ሆኖባቸዋል።
በ1960ዎቹ እና በ70ዎቹ ዘመናዊ የአልጋ ልብሶች ለጥሎሽ በቂ ነበሩ።
በ80ዎቹ ደግሞ እንደ ቴሌቪዥን እና ፍሪጅ ያሉ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ማበርከት መጀመሩን ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ያወሳል።
ቻይና ምጣኔ ሃብቷ መመንደግ ከጀመረችበት ከ1990ዎቹ ወዲህ ደግሞ ጥሎሽ በመኪና እና ቤት ተለውጧል።
እናም ሃብት ያላካበተ ቻይናዊ የማግባት እድሉ እየተመናመነ በመምጣቱ ጥሎሽ የማይጠይቅ ቤተሰብ ያላትን የትዳር አጋር ፍለጋ ወደ ጎረቤት ሀገራት ማማተር ይዟል ነው የሚባለው።
የ33 አመቷ ወጣት ድርጊትም ከነዚህ ወገኖች ትችትን ማስተናግዱ ተጣባቂ ነው። በርካቶች ግን የራሷን ህይወት ለታናሽ ወንድሟ መስዋዕት ያደረገች በሚል አሞካሽተዋታል።