ለ75 ዓመታት በትዳር የኖሩት ጥንዶች በሰዓታት ልዩነተ ህይወታቸው አልፏል
በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎቹ ጥንዶች በ9 ሰዓታ ልዩነት ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል
የጥንዶቹ የቀብር ስነ ስርዓት መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል
በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን ለ75 ዓመታት በትዳር የኖሩት ጥንዶች በሰዓታት ልዩነተ ህይወታቸው ማፉ ተሰምቷል።
ነገሩ የሆነው ምእራብ ሸዋ ዞኗ ኢሉ ገላን ወረዳ ሜታ ኪዳነ ምህረት ቀበሌ ሲሆን፤ ጥንዶቹ ላፉት 75 ዓመታት በትዳር አብረው አሳልፈዋል።
አቶ ጊሎ ቶሌራ የ100 ዓመት እድሜ ባለጸጋ ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ወይዘሮ ጥሩ በንቲ ደግሞ የ90 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ እንደነበሩ ኢሉ ገላን ወረዳ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በፌስቡክ ገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
75 ዓመታትን አብረው በትዳር ያሳለፉት ጥንዶቹ ህይወታቸውም በሰዓታት ልዩነት ማለፉ በርካቶችን አስገርሟል።
ጥንዶቹ በጤና እክል ሳቢያ ህክምና ላይ ቆይተው ህይወታቸው ያለፈ መሆኑንም የወረዳው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አስነብቧል።
በዚህም መሰረት ጥንዶቹ በ9 ሰዓታት ልዩነት መስከረም 5 2014 ዓ.ም ምሽት እና በማግስቱ መስከረም 6 2014 ዓ.ም ህይወታቸው ማለፉን አስታውቋል።
የሁለቱም ጥንዶች የቀብር ስነ ስርዓት መስከረም 7 ቀን 2014 ዓ.ም ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት መፈጸሙ ታውቋል።
አቶ ጊሎ ቶሌራ እና ወይዘሮ ጥሩ በንቲ በትዳር በቆዩባቸው ጊዜያት 8 ልጆችን አፍርተዋል።