የአለማችን የስለላ ተቋማት መሪዎች በሲንጋፖር ሚስጢራዊ ስብስባ አደረጉ
የአሜሪካ፣ ቻይና እና ህንድ የስለላ ተቋማት ሃላፊዎች በተሳተፉበት ውይይት ሩሲያ አልተገኘችም ተብሏል
ሲንጋፖር የእስያ ሀገራት የደህንነት ጉባኤን እያስተናገደች ነው
ከ20 በላይ ሀገራት የስለላ ተቋማት ሃላፊዎች በሲንጋፖር ሚስጢራዊ ስብሰባ ማድረጋቸው ተነገረ።
ምክክሩ ሲንጋፖር እያስተናገድችው ከሚገኘው የእስያ ሀገራት የደህንነት ጉባኤ (ሻንግሪ - ላ ምክክር) ጎን ለጎን መካሄዱንም ሬውተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።
አሜሪካ በብሄራዊ ደህንነት ዳይሬክተሯ አቭሪል ሄነስ የተወከለች ሲሆን፥ ቻይናም ከዋሽንግተን ጋር ግንኙነቷ ቢሻክርም በሲንጋፖሩ ሚስጢራዊ የደህንነት ስብሰባ ተሳትፋለች ተብሏል።
ህንድም በደህንነት ተቋሟ የጥናትና ምርምር ክፍል ሃላፊ ሳማንት ጎይል አማካኝነት ተወክላ መሳተፏን ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ለስብሰባው ቅርበት ያላቸው ሰዎች ነግረውኛል ብሏል ሬውተርስ።
ይሁን እንጂ አሜሪካም ሆነች ቻይና እና ህንድ ስለሚስጢራዊው ስብሰባ ማረጋገጫ አልሰጡም።
የሲንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሀገራት ከሻንጋሪ - ላ ጉባኤ ጎን ለጎን የሁለትዮሽ ምክክር ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከመጥቀስ ውጭ ስለ ስለላ ተቋማቱ ምክክር ያለው ነገር የለም።
የዩክሬን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ቮልድሚር ሃቭሪይሎቭ በሻንግሪ - ላ የደህንነት ጉባኤ ቢሳተፉም በስለላ ተቋማት ሃላፊዎቹ ሚስጢራዊ ስብሰባ አልተገኙም ተብሏል።
ከ20 በላይ ሀገራት የስለላ ተቋማት ሃላፊዎች በታደሙበት ስብሰባ ሩሲያ አለመገኘቷንም ዘገባው አክሏል።
የአሜሪካ፣ ብሪታንያ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ የደህንነት ሹሞች “አምስቱ አይኖች” በሚል ስብስብ የስለላ መረጃዎችን ከመለዋወጥ ባሻገር በየጊዜው እንደሚመክሩ ይታወቃል።
በሲንጋፖር በሳምንቱ መጨረሻ እንደተካሄደው አይነት በርካታ ሀገራትን ያሳተፈ ምክክር ሲደረግ አልታየም ወይም አልተገለጸም የሚለው ሬውተርስ፤ በምክክራቸው ያነሱት ነጥብ አብዛኛው ሚስጢራዊ ቢሆንም የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ምንጮቹን ተቅሶ አስነብቧል።
ሲንጋፖር የ2023ቱን የሻንግሪ - ላ ጉባኤ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ እያስተናገደች ነው።
ከ49 ሀገራት የተወከሉ ከ600 በላይ የደህንነት ባለሙያዎች እና የሀገራት መሪዎችም በዚሁ ስብሰባ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።